ታላቁ ንጉስ ጎቤ(1838-1878 ዓ.ም/እ.አ.አ)
በተመስገን ወ/ፃዲቅ
“ዎላይታ ሀብታም ሀገር ነበረች”
ከ50 በላይ ነገስታት በተፈራረቁባት ዎላይታ የንጉስ ጎቤ ታሪክ በሰፊው ሲወራ ብዙም አንሰማም::የታሪክ አዋቂዎችና አባቶቻችን አልፎ አልፎ ከሚያወሩት በስተቀር ትውልዱ ስለ በሳሉ ንጉስ ጎቤ እምብዛም አያውቅም::ታላቁ የዎላይታ ንጉስ ጎቤ የእፎይታ ንጉስ በሚባል ይታወቃሉ::ክብርን ከግርማ ጋር የተላበሱ በአካባቢው መንግስታት ዘንድ ሲጠሩ የኖሩ ንጉስ ነበሩ::
ንጉስ ጎቤ ከአባታቸው ከአማዶ ዳሞቴና ከእናታቸው ላጂቤ በ1797 ዓ.ም ተወልደው በ1878 ዓ.ም በ87 ሳይሞቱ እንዳልቀረ የታሪክ ምሁርና የክብር ዶክተር የሆኑት ዘብዴዎስ ጫማአ ይናገራሉ::ታላቁ ንጉስ ጎቤ ዘውድ (ካላቻ) ደፍተው የነገሱት ከ1838-1878 ዓ.ም ድረስ ባሉት 40 ዓመታት ውስጥ ነው(ቁጥሩን ወደ 48 ከፍ የሚያደርጉም የታሪክ ምሁራን አሉ):: ቤተ-መንግስታቸውን ከዳሞታ ተራራ በስተምስራቅ እተራራው ግርጌ ላይ አድርጎ ዎላይታን መርተዋል::
በዲፕሎማሲ የሚታወቁት ንጉስ ጎቤ ከጅማው ንጉስ አባጅፋር ጋርም ለመወዳጀት አስበው ተሚማ ዲግቴ የተባሉትን የአባጅፋር ሴት ልጃቸውን አግብተው ልጆችን ወልደዋል::
የንጉስ ጎቤ ዘመን ዎላይታ ጥጋብ በጥጋብ የሆነችበት ዘመን እንደነበር ያገሬው ሰው በየአጋጣሚ ሁሉ ያነሳል ምርትም እንደ በቆሎ ያሉት እያንዳንዱ ተክል ከ 7-12 ራስ የሚይዝበት ከልክ በላይ ሆኖ ሌሎች የጎረቤት ሀገራት የሚያስቀና አገር ነበር::አፄ ምንሊክ በወቅቱ የጎቤን ዝናና የዎላይታ ሀብታም የመሆን ጉዳይን ለመሰለል ሰላይ ይልኩ እንደነበረና በአንድ ወቅት በጦር ለመያዝ ሞክሮ እንዳልተሳካላቸው አባቶች ያወጋሉ::
በንጉስ ጎቤ ወቅት ዎላይታ ከጎረቤት ሀገራት ጋር
የነበረው ሰላማዊና ስልጡን ግንኙነት ከእሳቸው በፊት ይነሳ የነበረውን ግጭት ጭራሹን አጥፍቷል:: ዎላይታም በጣም ሀብታም ሀገር ሆኗል::እንዲያውም በወቅቱ “ጎቤ ጊፋታ”ይባል ነበር::ሁለት ቤተሰብ አንድ በሬ ለጊፋታ ያርድ እንደነበረ ይነገራል::
ታላቁ ንጉስ ጎቤ ዎላይታን በጥጋብ ከመሩ በኃላ በጠና ታመው በመሞታቸው መንበረ ስልጣናቸውን ጀግናው ንጉስ ጦና ተረክበዋል::በጎቤ ወቅት የተሞከረው የምንሊክ ዎላይታን የመያዝ ዘመቻ በጦና ጊዜ እያየለ መጥቶ በከባድ ጦርነት መደምደሙ ይታወቃል::
“ዎላይታ ሀብታም ሀገር ነበረች”