እሱ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ጀሌዎቹ ጭምር መወገድ አለባቸው!!!
መድህን ማርጮ (ዶ/ር)
ሌቦቻችሁን አንሷቸው፤ ግን እባካችሁ እንደገና ሌላ አዲስ ሌባ አታምጡብን፡፡ ሰው አጥታቸሁ በጣም ከተቸገራችሁ ሌባ ከሚሾም ዩኒቨርሲቲው እንዲሁ ያለ ፕሬዚዳንት ቢተው ይመረጣል፡፡
በጣም የሚቀፈው የኋላ ኋላ ሌብነት ላይ ለመሰማራት እስከ 3ኛ ዲግሪ እየተማሩ ሩብ ምዕተ-ዓመት (25 ዓመት) የሚጠጋ ጊዜ የማጥፋት ነገር ነው፡፡ የበለጠ የሚዘገንነው ደግሞ ከ20 ዓመት በላይ በድሃ ህዝብ ገንዘብ ከተማሩ በኋላ ፍደል ለመቁጠር ዕድል ተነፍገው ጎዳና ላይ ከወጡት ህጻናት ጎሮሮ ገንዘብ መመንተፍ፡፡ የተማርክ ሌባ ስትሆን ባለዕዳ ብቻ ሳይሆን አንተም ራስህ የትውልድ፤ የሀገርና የታሪክ ዕዳ ነህ፡፡
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ዝርፊያ ዙሪያ ደጋግሜ ጽፍያለሁ፡፡ ቀፋፊ የሌብነት ሪከርድ ካላቸው በርካታ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነው፡፡ በሀገራችን እጅግ ከፍተኛ ምዝበራ ከሚካሔድባቸው ቦታዎች መካከል ዩኒቨርሲቲዎች ግምባር ቀደሞች ናቸው፡፡ከምክንያቶቹ መካከል ደግሞ ግምባር ቀደም የሚሆነው ሀገሪቱ ውስጥ ያሉት አብዛኛዎቹን ዩኒቨርሲቲዎች የሚመሯቸው ፕሬዚዳንቶች የገዢው ፓርቲ ቁልፍ አባላት ከመሆናቸውም በላይ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ካልሆነም የክልል ም/ቤት አባል በመሆን ያለመከሰስ መብት (ከለላ) የተጎናፀፉ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ከለላ ያለስጋት የመመዝበር ዕድል ይፈጥርላቸዋል::
የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትነትና ፖለቲካ ፓርቲ ጋብቻ እስካልፈረሰ ድረስ በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄደው ተቋማዊ ምዝበራ ይቀጥላል:: ይህ ጉዳይ ለመንግሥት የተሰወረ ነው ማለት አይቻልም:: መንግሥትም አሰራሩን ለማረም ገና ያልተዘጋጀ ለመሆኑ አንዱ ማሳያ አሁን በቅርብ ፕ/ር ብርሐኑና ዶ/ር ሳሙኤልን ራስ-ገዝ እየሆነ ነው ለተባለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአመራርነት መመደቡ ነው፡፡
ወደ ተነሳሁበት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሌብነት ምዝበራና አመራር ውድቀት ጉዳይ እንመለስ፡፡ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳን ፕ/ር ታከለ ታደሰ የደቡብ ብልጽና እና የፈረሰው ደቡብ ብ/ብ/ህ ክልል ምክር ቤት አባል ናቸው፡፡
በዚህ ስልጣን ተከልለው ዩኒቨርሲቲውን የመዘበሩትና ያስመዘበሩትን ዝርፍያ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሪፖራት መሰረት በማድረግ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 13 ቀን ይፋ በማድረግ ስለዚህ ልቅ ዘረፋና ምዝበራ ከ1 እስከ 3 ወር ጊዜ ውስጥ ከፕሬዚዳንቱና እሳቸው ከሚመሩት ተቋም ይፋ ምላሽ ማግኘት የሚገባቸው ውሳኔዎች አሳልፎ እንደ ነበር እናስታውሳለን:: የቋሚ ኮሚቴው (የእነ ክርስቲያን ታደለ) የመጋቢት 13ቱ መግለጫ የተመለከተ ቪዲዮ ሊንክ ከሥር አለላችሁ::
ከውሳኔዎቹም መካከል፤
1. ትምህርት ሚኒስቴር በመንግሥት የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሀላፊነት አላግባብ ተጠቅመው በኦዲት ግኝቱ የተገለፁትን የአሰራርና የአመራር ቅሌቶች የፈፀሙ የዩኒቨርስቲው ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ላይ ተገቢውን የእርምት እርምጃ ወስዶ በ10 ቀናት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያሳውቅ።
2. የፍትህ ሚኒስቴር በመንግሥት የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሀላፊነት አላግባብ ተጠቅመው በኦዲት ግኝቱ የተገለፁትን የአሰራርና የአመራር ቅሌት የፈፀሙ የዩኒቨርስቲው ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ላይ መረጃ አደራጅቶ በ3 ወራት ውስጥ ክስ እንዲመሠርት።
3. ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲውን መዋቅር በመፈተሽ በመንግሥት የተጣለባቸውን ከፍተኛ ሀላፊነት አላግባብ ተጠቅመው በኦዲት ግኝቱ የተገለፁትን የአሰራርና የአመራር ቅሌቶች የፈፀሙ የዩኒቨርስቲው ሀላፊዎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ ወስዶ በ3 ወራት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው እንዲያሳውቅ።
4. ዩኒቨርስቲው ከተሰጠው ስልጣን ውጭ በራሱ ባወጣው መመሪያ መሠረት ክፍያዎችን መፈፀም በአስቸኳይ እንዲያቆምና እስካሁን አላግባብ የተፈፀሙ ክፍያዎችንም ተመላሽ እንዲያደርግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ታከለ በፕሬዚዳንትነት ስልጣን ላይ እያሉ ከላይ ፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተጣርቶ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት ወጪ አሥተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 13 ቀን ይፋ የተደረገው ለሰሚ ጆሮ የሚከብድ ገንዘብ ተሰረቀ፤ተዘረፈ፤ ተመዘበረ፡፡
ታከለ በፕሬዚዳንትነት ስልጣን ላይ እያሉ July 2022 በዩኒቨርሲቲው ሶሻል ሳይንስ እና ሂውማኒቲስ ኮሌጅ ሥር 115 ሰዎች በተካፈሉበት በተባለው አንድ ስልጠና 5.4 ሚልዮን ብር የኪስ ገንዘብ ተመዝብሯል፡፡
በዚህም በአንድ ሰው እስከ 400,000 ብር የሚደርስ የተሳትፎ/የኪስ ገንዘብ ክፍያ ተፈፅሞ ነበር፣ በአጠቃላይ ለስልጠናው ተሳታፊዎች የተከፈለው ክፍያ 5,450,000 ብር (አምስት ሚልዮን አራት መቶ ሀምሳ ሺህ ብር) ውስጥ 4 ሚልዮን ብሩ የተከፈለው የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አምስት ሰዎች ጨምሮ ለ10 ተሳታፊዎች ሲሆን በዚህም ለእያንዳንዳቸው 400,000 ብር ተሰጥቷቸዋል፡፡
ታከለ በፕሬዚዳንትነት ስልጣን ላይ ሆነው ሚልዮነ-ሚልዮናት ብር እየመዘበሩና እያስመዘበሩ የዩኒቨርሲቲ ቲችንግ ሆስፒታል ማዋለጃ ክፍል በበጀት እጥረት ለአዋላጅ ሀኪሞች እጅ መታጠቢያ ሳሙናና ጓንት መግዣ ጠፋ ተብሎ እጅግ በርካታ እናቶች ተገቢውን የሀኪም እርዳታ ማግኘት ሳይችሉ ወሊድ ላይ ሞተዋል፡፡
ታከለ በፕሬዚዳንትነት ስልጣን ላይ እያሉ በዩኒቨርሲቲው የ2015 ዓ.ም ማጠቃለያ ውጤት ከ45 የትምህርት ክፍሎች 2,987 ተማሪዎች Exit Exam ተፈትነው 1,887 (63.17%) ወድቀዋል፤ 1,100 (36.83%) ብቻ አልፈዋል፡፡ ይህም ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ዩኒቨረሲቲዎች መካከል ተቋሙን ውራና ጭራ ያደርገዋል፡፡
ታከለ በፕሬዚዳንትነት ስልጣን ላይ እያሉ በእሳቸው ወቅት ቢብስም እሳቸውና ከእሳቸው በፊት ሥልጣን ላይ የነበሩት አመራሮች በፈጠሩት ቅሌት የዩኒቨርሲቲው ስም ከስኬት ይልቅ ከውድቀት ጋር በጥብቅ በመቆራኘቱ በ2015 ዓ/ም ሀገሪቱ ውስጥ ባሉት ዩኒቨርሲቲዎች አዲስ-ገቢ ተማሪዎች ሲደለደሉ ወደዚህ ዩኒቨርሲቲ ለመመደብ በራስ ምርጫ ፍላጎት ያሳየ አንድም ተማሪ መጥፋቱን ትም/ት ምንስቴር በወቅቱ ይፋ አደርጓል፡፡
ማጠቃለያ የተከበሩ እነ አቶ አህመድ ሸዴ ሆይ፡- መንግስትዎ እኚህን ሰው ለማስወገድ ማሰቡ እርግጥ ከሆነ አፍጥኑት፡፡ ታዲያ ማስወገድ ያለባችሁ እሱን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ጀሌዎቹ ጭምር እንዳለ ኔትወርኩን መሆን አለበት፡፡ ደግሞም አንስታችሁ ስታበቁ ሌላ አዲስ ሌባ እንዳታመጡብንና እንዳንታዘባችሁ ተጠንቀቁ፡፡