የወላይታ ሕዝብ ድሮ “ቦሌ ሻዮዴ ባ ምሻው ባሽያ ሳኤስ” ይል ነበር ፤ ዛሬ ግን ታሪክ ተቀየረ!!!
ነሐሴ 09 2012ዓ.ም
ትርጉም፡ አንበጣ ስቆሉት ለሕመሙ ምጣድን ይነክሳል ማለት ነው።
በተፈጥሮ ሕግ ማንኛውም ሕይወት ያለው ፍጡር ጥቃት በሚደርስበት ወቅት አስቦበት (Consciously) ወይም ደመ- ነፍሳዊ በሆነ ስሜት (Emotionally) ጥቃት እያደረሰበት ባለው አካል ላይ አፀፋዊ ምላሽ መስጠት ራስን የመከላከል ወይም አፀፋዊ እርምጃ መውሰድ ተፈጥሯዊ ነው። ሕልውናውን የማስጠበቅ መብትም ነው።
ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ትዕዛዝን የሰጠው አካል ወይም አካላት ማንም ይሁኑ ማን፤ ከሰኞ ነሐሴ 4 እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ አገርን እና ዜጎቿን ከውጭ እና ከውስጥ ወራሪ እንዲከላከል የተደራጀው የመከላከያ ሰራዊት አልሞ ተኳሽ ኮማንዶ ጦር በንፁሓን የወላይታ ሕዝብ ላይ ምናልባትም በአገሪቷ ታሪክ አቻ የሌለው ጭፍጨፋ አካሂዷል። በርካታዎችን አካለ ጎዶሎ አድርጓቿዋል።
እንዲህ ያለ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ስፈፀምበት ማንም የሰው ልጅ ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ የመስጠት አቅም ባይኖረውም ቅሉ እየሞተም ቢሆን የቻለውን ያህል አፀፋዊ ምላሽ አስቦም ሆነ በደመ-ነፍሳዊ ስሜት ለመውሰድ ይገደዳል።
ነገር ግን የወላይታ ሕዝብ እንዲህ ያለ አረመኔያዊ ጭፍጨፋ እየተፈፀመበትም እያለም ግን ገዳዮቹ ላይ አንድም ድንጋይ ወርውሮ አላቆሰለም። በሰላማዊ መንገድ ስሜቱን እየገለፀ ያለው ወንድሙ በፊቱ በጥይት እየተቆላ ሲወድቅ እና ሲሞት እያየ እንኳን ወደኋላ ሳያፈገፍግ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ፅናት ሰላማዊ ትግሉን ወደፊት በመግፋት አኩሪ ድል አስመዝቧል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በአገሪቷ ውስጥ አንድ ብሔረሰብ ወይም የተወሰኑ አካላት አንዳች ተቃውሞ ወይም የመብት ጥያቄ ለማሰማት በሚል ሰበብ ወደ አደባባይ በሚወጡበት ግዜ ዘር እና ሐይማኖት እየለዩ ጥቃት በሚፈፀሙበት አገር፤ ሐብት እና ንብረት በሚያወድሙበት አገር ውስጥ አንዲት ብርጭቆ እንኳን ሳይሰብሩ፣ አንድም ሰው ላይ በዘር ወይም በሐይማኖት ለይተው ድንጋይ ሳይወረውሩ፣ “ቦሌ ሻዮዴ ባ ምሻው ባሽያ ሳኤስ” የተባለውን አባባልም ሽረው፣ ከላይ የተጠቀሱትን የተፈጥሮ ምላሾችንም አሸንፈው፤ ለአገራችን ሕዝቦች እና ለመላው ዓለም ሕዝብም የወላይታ ሕዝብ የደረሰበትን ስልጣኔ፣ ስሜትን በታላቅ የስብዕና ልዕልና (Supper Conscious Personality) የማሸነፍ ጥበብን አሳይቷል። በዚህም በወላይታ እየሆነ ያለው የሕዝብ ትግል እንደሌላው አካባቢ አንዳች የዘር ጥቃት ልፈፀም ይችላል፣ ሐብት ንብረት ልወድም ይችላል በሚል ግምት በዝምታ እና በአንክሮ ሲከታተሉ የነበሩት በሙሉ የትግሉ ፍፃሜ ባላሰቡት እና ባልጠበቁት ሁኔታ በሰላም መጠናቀቁን በማየት ለወላይታ ወጣቶች እና ለሕዝብ በሙሉ ያላቸውን አክብሮት እና አድናቆት እያሰሙ ይገኛል። በዚህ እኔም እንደአንድ ወላይታ ኩራት ተሰምቶኛል። ሌላው አሁን አሁን በአገራችን የገዛ መብትን ወይም ተቃዉሞ ለማሰማት የሌላ ንፁሐን ደም ማፍሰስ እና ሐብት ንብረት ማውደምን የሰርክ ተግባር አድርገው እየፈፀሙ ላሉት አካላት መማር የሚፈልጉ ከሆነ እና ከፈለጉ ትልቅ ትምህርት ሰጥቷል።
አሁንም፣ ነገም ለዘላለምም ድል፣ ክብር እና ፍትሕ ለወላይታ ሕዝብ !!!
ዘላለማዊ ክብር እና ሞገስ በግፍ ያለፍርድ ለተገደሉት የወላይታ ሰማእታት !!!
አሁንም የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት !!!!