የፈረንጅ ሲሆን ከላይ የአፍሪካ ሲሆን ከዲያቢሎስ ነው ካልተባለ በቀር
ተመስገን ማርቆስ ኪንዶ (ዶ/ር)
የክርስቶስ ወንጌል መሰበክ የጀመረበት ወቅት ላይ መጀመሪያ ወደ ቤተክርስቲያን የመጡት አይሁድ ነበሩ፤ ሃዋሪያቱም እንዳሉ አይሁድ ናቸው፡፡ ወንጌሉ ሲሰፋ አህዛብም በአይሁድ ላይ ተጨምረው ቤተክርስቲያን ማደግ ጀመረች፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት የባህል ግጭት ተከሰተ፡፡ አይሁዶቹ የእነሱን ስርአት ያልተከተለ ሰው እንዴት ክርስቲያን ይሆናል ብለው ቀወጡት፡፡
እንዲያውም ምእመኑ መሪዎቹን ተቆጣ በዚህ ጉዳይ፡፡ የሃዋሪያት ስራ ምእራፍ አስራ አንድ ላይ ያለ ታሪክ እንዲህ ብሎ ይጀምራል፦ “ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ አሉት። ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ።”
ታሪኩን ጨርሳችሁ ማንበብ ትችላላችሁ ግን ጭብጡ ክርስቲያን ለመሆን አህዛብ በክርስቶስ አምነው ትምህርቱን መከተል እንጂ የአይሁድ የምግብና ሌሎች ስርአቶች ግርዛትንም ጨምረው መከተል አስፈላጊ እንዳልሆነና የአይሁድን ባህል ከዚያ ባህል ባልመጡ ክርስቲያኖች ላይ መጫን አስፈላጊ እንዳልሆነ ነው ጴጥሮስ ያስተማረው፡፡
ለነገሩ ጴጥሮስ ራሱ ትንሽ በዚህ ጉዳይ ሊንሸራተት ዳር ዳር ብሎ ነበር፤ ለአህዛብ ወንጌሉን ማድረስ ላይ በወቅቱ ትልቁን ድርሻ ይዞ የነበረው ጳውሎስ ባይወቅሰው፡፡ ይህን ጉዳይ ጳውሎስ በገላቲያ ምእራፍ ሁለት ላይ ያብራራል፡፡ “ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ። ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና። አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት።”
***
ሃይማኖትና ባህል ከላይ ከላይ ሲታዩ የተለያዩ ነገሮች ቢሆኑም ሙሉ ለሙሉ መነጣጠል የምንቻላቸው ነገሮች አይመስሉኝም፤ የሃይማኖት ልምምዶች ወደሃይማኖቱ አስቀድመው በመጡ ሰዎች ባህል ይቃኛል፡፡ ይህ ሲሆን ሃይማኖቱ ሲሰፋ ከሌላ ባህል የሚመጡ ሰዎች የሚስተናገዱበት መንገድ እንደ ጳውሎስ በጥንቃቄ ካልተደረገ ለአላስፈላጊ ግጭት ይወስዳል፡፡ የሰባኪው ባህል ሃይማኖታዊ ተቀባይነት ይዞ የተሰባኪው ባህል እንደጣኦት አምልኮ የሚታይበት ሁኔታ ሰሞኑን በተለይም በደቡብ ኢትዮጲያ የሚከበሩ በአላት ጋር ተያይዞ ይታያል፡፡
የአውሮፓ ካላንደር አዲስ አመት የሚጀምርበት ጃንዋሪ ስሙ ራሱ የመጣው በጥንታዊ ሮማ የጅማሬዎች አምላክ ከባለሁለት ፊቱ ጃነስ ነው፡፡ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጲያዊያን የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በጃንዋሪ የአውሮፓ አዲስ አመት ሲከበር አንድም “ይህ በሮማ ጣኦት የተሰየመ ወር በክርስቲያኖች እንደ አዲስ አመት መከበር የለበትም” አይሉም፡፡ በቤታቸውም ሆነ በቤተእምነታቸው ፊሽታ ወይ አምልኮ ሲያደርጉ ፎቶ ይለቁልናል፡፡ ከነዚህ መሃል አንዳንዶቹ ልክ የኢትዮጲያ ብሄረሰቦች በራሳቸው የዘመን አቆጣጠር አዲስ አመት የሚሉት ሲመጣ የጣኦት አምልኮ መሆኑን መስበክ ሲያያዙ ግር ይለኛል፡፡
ከቅኝ ግዛት በፊት እያንዳንዱ የአፍሪካና የኢሲያ ሃገር የራሱ የዘመን መቁጠሪያ እንደሚኖረው ለመገመት ኒዩክሊየር ሳይንቲስት መሆን አይጠይቅም፡፡ አሁን በአንድ ሃገር ስር ያሉ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎችም ያ ሃገር አሁን ያለውን ቅርጽ ከመያዙ በፊት የራሳቸው የዘመን መቁጠሪያ ቢኖራቸው ሊገርም አይገባም፡፡ ለመግባባት ሲባል በፍቃድ ወይም ደግሞ በግዛት ወቅት በመጨፍለቅ የተደበቁ አቆጣጠሮች አንጻራዊ ነጻነት ሲኖር ቢወጡ ቤተክርስቲያኖች “ጣኦት ጃስ ጃስ” የሚሉት ያስኬዳል? ምነው ጃነስን ጃስ የማይሉት?
እርግጥ ነው ምእመናን ባህል ነው ብለው አለማዊ ዳንኪራ፣ መጠጥ ወዘተ ውስጥ ከገቡ መወቀስ አለባቸው፤ ለአውሮፓ አዲስ አመት ለስላሳ የጠጣ የብሄሬ አዲስ አመት ነው ብሎ ቦርዴ ቢጠጣ ዝም መባል የለበትም፡፡ ግን ጥያቄው መሆን ያለበት አከባበሩ ላይ ነው እንጂ መከበሩ ላይ መሆን የለበትም፡፡
ለጨምበላላ፣ ለጊፋታ ወዘተ ህዝቡ “ከአመት አመት ያሻገረንን አምላክ እናመሰግናለን” ቢል ምስጋናውን ለትክክለኛው አምላክ እስካደረገ ድረስ ለጃነስ የሚያሸበሽቡ እነዚህኛዎቹን ለማውገዝ ሞራል ያላቸው አይመስለኝም፤ የፈረንጅ ሲሆን ከላይ የአፍሪካ ሲሆን ከዲያቢሎስ ነው ካልተባለ በቀር፡፡ ጳውሎስ በአንደኛው ክፍለዘመን የነበረው የብዝሃነት መረዳት የሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ሰዎች ላይ ይጉደል?