የወላይታ ሶዶ ከተማ መርካቶ ገበያ መቃጠል በጣም አሳዝኖናል!!

Wolaita Today

ታህሳስ 14 2013ዓ.ም

የወላይታ ሶዶ መርካቶ ገበያ የሁሉ መገበያያና የሁሉ ጓዳ መሆኗን የወላይታ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም የአካባቢው ሕዝቦች በተለይም ቁጫ፣ ጋሞ፣ ዳውሮ፣ ጎፋ እና ሌሎችም የሚያውቁትና የሚኖሩት እውኔታ ነው።

የወላይታ ሶዶ ከተማ የአካባቢው የንግድ ማዕከልና የሁሉ መገናኛ ከመሆኗ የተነሳ ሀብታሙም ድሃው ከተሜው ገጠሩ ተወደደ ረከሰ ከመርካቶ ገበያ የሚያጣው ኖሮ አያውቅም።

መርካቶ ገበያ ሰው ከሰው ሳይለይ የሁሉ የአካባቢው ሕዝቦች የጋራ የሥራ ማዕከልና የጋራ ሀብትም ምንጭ ነች።

ታዲያ ይህ ገበያ በየጊዜው ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ በእሳት ሲጋይና የድሃውንና የለፍቶ አዳሪው መተዳደሪያ አመድ ሲሆን እንደማየት የሚያሳዝን የለም።

ተመሳሳይ አደጋ በተደጋጋሚ ሲደርስ እያዪ ለዘላቂ መብትኼም አለመሥራት ሌላው አሳሳቢ ነገር ነው።

መንግስትም ሆነ የገበያው ንግዱ ማህበረሰብ ከባለፈው ክስተት በመማር በጋራ በመቀናጀት ለዚህ አደጋ ቅድመ ጥንቃቄ ና ዝግጅት እንዲሁም ተገቢ እርምጃ መውሰድ የአደጋ ምልክቶችም ሲታዩ አፋጣኝ የመከላከያና የመቆጣጠሪያ ዜዴዎችን በመጠቀም በንቃት አደጋዎችን ማጥፋት አሊያም መቀነስ ይቻል ነበር።

በቸልተኝነት ወይም በመዘናጋት የደረሰው ከፍተኛ አደጋ ለወደፊትም እንዳይከሰት ከዚህ በኋላ ልወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎች፤

============================

1)የተጎዱ ወገኖችን መልሶ የማቋቋምና የመካስ ሥራ ቶሎ መጀመር አለበት። ለዚሁም ሁሉ ሰው የየራሱን ድርሻ መወጣት አለበት። እያንዳንዱ ነጋዴ ከእለታዊ የንግድ እንቅቃሴ አልፎ ለዘለቄታዊ መብትኼና የጋራ ደህንነት መሥራት አለበት።

2) ገበያው በትክክለኛውና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በግንብ በተሠሩ ሱቆች እንዲደራጅ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ አለበት

3) የገበያው ዙሪያ ከመንግስትና ከነጋዴው ማህበረሰብ በሚዋቀር ጥምር ኮሚቴ እንዲተዳደር ቢደረግ

4) ገበያው መገበያያ ብቻ ሳይሆን የነጋዴውና የሕዝብ ሀብት ማከማቻም ስለሆነ ልዩ የመንግስት ጥበቃ ተመድቦ እንድጠብቅ ቢደረግ

5) ተቀጣጣይና የመፈንዳት ባህሪ ያላቸው ነገሮች ለአብነት ያህል ቤንዚን፣ ዘይት፣ኮስሞቲክስ ወዘተ በእንዲህ አይነት የገበያ ማዕከላት እንዳይሸጡ በጥብቅ መከልከልና መቆጣጠር ያስፈልጋል። መንግስትም በገበያው ያሉ የንግዱ ማህበረሰብ ለጋራ ደህንነት ሲሉ ከወትሮ በተለየ መልኩ በዚህ ጉዳይ መሥራት ይጠበቅባቸዋል

6) ሁሉን ነገር በአንድ ማዕከል ማከማቸት ለአደጋ ተጋላጭ ከማድረግ አልፎ ለከፍተኛ ውድመት ስለሚዳርግ አደጋዎችን ለመቀነስም ሆነ የግብይይት አገልግሎትን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶችን በማጠናከር በየክፍለ ከተማው ደረጃቸው ከፍ ያለ ተጨማሪ የገበያ ማዕከሎችን መገንባት ተገቢ ነው እንላለን።

ለተጎዱ ወገኖች እንድረስላቸው!!!

ፈጣሪ ሁሉንም ያፅናና፣ ጉዳቱ የደረሰባቸውን በበረከቱ ይካሳቸው!!!

ቁሕዴፓ 12/2013 ዓ.ም