ዜግነትና ብሔር ያልገደበው የአባ ጂኖ የዎላይታ ፍቅር
በአምሳሉ መሰኔ (ቃቆ)
ታህሳስ 7 2013ዓ.ም
ቄሲ አባ ጂኖ ቤናንቲ በ1963 ዓ/ም ከጣልያን ሀገር ከጓደኞቻቸው ጋር ገና በለጋ ዕድሜያቸው (27)ጉዞ ወደ ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ ከዛም ወደ ሃምሳ ነገሥታት ምድር ወደ ዋጃ ወደ ዱቦ ሉርድ ማርያም መገኛ ዎላይታ አቀኑ፡፡
እነ ሪሞ ቺያቲን የማረከው የሀገረው ሰው እንግዳ አክባሪነት ና ፍጹም ጨዋነት ማርኳቸው ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ኃላ ለመመለስ ወኔ አጡ፡፡ በዎላይታዎች ፍቅርና ታሪክ ተማረኩ፤ የዋጃዋ ኪ/ምህረትን ብለው መቀበሪያዬም እዚሁ ይሆናል በፍጹም አልሄድም አሉና ቀሩ፡፡ ቄሲ አባ ጂኖ ቤናንቲ በግል ካላቸው ደግነት መነሻ አብሯቸው የሰሩ ያገለገሉ ሁሉ የሚወዷቸዉ ታላቅ ትሁት አባት ነበሩ፡፡
- በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በቀድሞ ሶዶ-ሆሳዕና ሀገረ ስብከት ብዙ ቦታ ተመድበው መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ሰጪ የሆኑ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡
- በ1972 ዓ/ም የሾኔ ቅ/ጴጥሮስ-ጳውሎስ ት/ቤት በኃላፊነት
- የሀገረ ስብከቱ አቡን የአቡነ ዶሚኒኮ የቅርብ አማካሪና በፀሐፊነት
- የታላቋ ዱቦ ሉርድ ማርያም አዳሪ ት/ቤት (Boarding school) በኃላፊነት
- የመጨረሻ ማረፍያቸው ወደ ሆነችው ወደ መረጧት ዋጃ ኪዳነ ምህረት ቤ/ያን ተመድበው በኃላፊነት ብዙ ሥራዎችን ሰርተዋል
- ቀነፉ ቅ/ፍራንቺስኮስ ኃላፊ በመሆን በሥሩ በነበሩ በገሱባ ከተማ መዋዕለ ሕጻናት (አሁን በመንግሥት እጅ የሚገኝ)፣ ፋቃቃ ቅ/ገብርኤል ት/ቤት አስገንብተዋል
- የኢትዮጵያ ካፑቺን ማህበር ም/ኃላፊና የሶዶ ቆንቶ ታላቁ ገዳም ዋና ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል
- በሌ ፍልሰታ ማርያም ኃላፊ በነበሩበት ወቅት የካህናት መኖሪያ ያስገነቡ በተለይ በግል ጥረታቸው ብዙ ሚሊዮኖችን የፈጀውን የመብራት አገልግሎት ከተማው እንዲያገኝ የድርሻቸውን ተወጥተዋል
- በ1977 ዓ/ም ድርቅ የተቸገሩና የተራቡ ዜጎቻችንን እንደ መንፈሳዊ አባትነታቸውና ደግነታቸው ደግፈው ብዙ ረድተዋል፡፡ ብዙ የአባ ወዳጆች ይህንን ጉዳይ ከፍ ባለ ደረጃ ያነሳሉ፤ ያመሰግናሉ፡፡
ዎላይታ ከዳሞታ እግር ኳስ ቡድን ጀምሮ በሀገር ደረጃ የገነነ ስም ያላቸውን ስፖርተኞች ያፈራ አከባቢ መሆኑን ቄሲ አባ ጂኖ ተረድተውና ተመልክተው እነ ታምሩ ሙሉጌታ ( የብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና አሰልጣኝ የነበረ) እነ ሙሴ ሙንኤ እነ አብርሃም ባልቻ እነ በሽር ሴባ እነ እሸቱ ታፈሰ እነ አብርሃም ጩርፎ እነ ዘነበ ፍስሃ ወዘተ ያፈራው ዎላይታ እንዴት የእግርኳስ ቡድን ያጣል? በሚል ቁጭት ተነሳስተው ኃያሉን የዎላይታ ቱሣ እግር ኳስ ቡድንን መሠረቱ፡፡
በስፖርቱ ዘርፍ በራሳቸው ኃላፊነት ያቋቋሙት ኃያሉ ዎላይታ ቱሣ ገና በለጋ ዕድሜው በ1989 ዓ/ም በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ደቡብ ክልልን በመወከል ጂማ በተደረገው ውድድር የወቅቱን ኃያል ቡድን ኒያላን በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሶ አልማ (አማራ ልማት ማህበር) ቡድንን 1፡0 በማሸነፍ የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድር አሸናፊ ሆነ፡፡
በዚህም በቄሲ አባ ጂኖ የሚመራው ዎላይታ ቱሣ ስምና ዝና ከፍ ባለ ደረጃ ሲወራ ሲነገር ቆየ፡፡ ቡድኑም ኢትዮጵያን ወክሎ የመጫወት ዕድል በማግኘቱ ራሱን በብዙ መልኩ ሲያደራጅና ሲዘጋጅ ቆየ፡፡ በተለይ 1990 ዓ/ም ከአርባምንጭ እርሻ ይሁን ከነማ ጋር ሶዶ ከተማ በተደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሜዳ የነበሩ በርካታ የውጭ ዜጎች ፈረንጆች ከጁቬንቱስ ክለብ ጋር በአጋርነት ለመስራትና ሶዶ ላይ እጅግ ዘመናዊ ስታዲየም ለቡድኑ ለመገንባት ቃል ገብተው ነበር፡፡
በ1990 ዓ/ም በአፍሪካ የኮንፌዴሬሽን ካፕ ውድድር ኢትዮጵያን የወከለው ዎላይታ ቱሣ ከኤርትራው ቀይ ባህር ቡድን ጋር ዕጣ ደርሶት የመጀመሪያ ጨዋታ ጥር 24 ቀን 1990 ዓ/ም አ/አ ስታዲየም አድርገው 2:0 ተሸንፈው በመልሱ ጨዋታ አሥመራ ላይ 3:3 በመለያየት በደርሶ መልስ ውጤት ወደ ቀጣይ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል፡፡
ይህን ኃያል ቡድን አባን ደግፎ ይዞ መቆየት አስፈላጊ የነበረ ቢሆንም ተጫዋቾች ለተሻለ ጥቅም ወደ ተለያዩ ክለቦች ለመጫወት ሄዱ፡፡ለምሳሌ ፦ ኢብራሂም ረሽድ (ቃቆ)፣ ሙሴ ጳውሎስ፣ ጌታሁን ታደሰ (የቅ/ጊዮርጊስና ብሔራዊ ቡድን በረኛ የነበረ)፣ በቀለ ባልቻ (ፔሌ) ወዘተ፡፡ ነገር ግን አባ ጂኖ ታዳጊዎችን በማሳደግ ከነባሮቹ ከእነ አይደክመው ጀግና አምበል አሰፋ ሆሲሶ ጋር አጣምረው ሁለተኛውን የቱሣ ቡድን ይዘው ቀጥለዋል፡፡ ከሁለተኛ ትውልዶች መካከል ዳግም ዝናዬ፣ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ (ማሜገላ)፣ ተከተል ተሾመ፣ ቤዛ ዘለቀ፣ ተራማጅ ማቴዎስ፣ መላኩ ማቴዎስ ምንውየለት ለማ፣ ዘላለም ማቴዎስ፣ ሪያድ ካሊድ፣አሸናፊ ታደሰ፣ ዮፍታሔ ገ/ስላሴ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡
አባ ጂኖ የዎላይትኛ ሙዝቃ ያለውን እምቅ የማዝናናት አቅም በመረዳት የዎላይታ ቱሣ ባህላዊና ዘመናዊ ባንድ በማቋቋም ለዛሬዎቹ ጀግኖቻችን ለእነ ካሙዙ ካሣና ስማገኘሁ ሳሙኤል እንዲሁም በርካታ ተወዛዋዦች መፈጠርና በሙዚቃው ዓለም መንገሥ የመጀመሪያ ምክንያት ሆነዋል፡፡
ለሰብአዊነት ድንበር የለውም፤ ሰው ለመርዳታ ሰው መሆን ብቻ በቂ መሆኑን በተግባር ላሳዩን መንፈሳዊ ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን የሕዝባችንን ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች ላይ ከሀገሬው ሰው በላይ ተቆርቋሪ ለነበሩ ጀግና አባት አንድም ቀን አስታዋሽ ኖሮ በሚገባቸው ደረጃና ልክ ያመሰገነ ያበረታታ የለም፡፡ አሁንም ቢሆን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሚመጥናቸው ደረጃ ለአባ ጂኖ መታሰቢያ የሚሰራበትን ወይም የሚሰየምበትን ሁኔታ ያመቻቻል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለሚሄድ የሚደረግ ሽልማት ለሚመጣው ማበረታቻ ጉልበትና ኃይል ነውና፡፡
የዎላይታ ቱሣ እና የሶዶ ሲቲ ጤና ስፖርት ቡድን አባላት ለአባ ጂኖ ወደ ኢትዮጵያ ምድር የመጡበትን 50ኛ ዓመት የዛሬ ወር አከባቢ ማክበራቸውና ስጦታ ማበርከታቸው ደስ የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡
ሲጠቃለል ቄሲ አባ ጂኖ ቤናንቲ ድንገት ተማርከው በቀሩበት ዎላይታ ምድር 50 ዓመታትን ኖረው አፈር ነህና ወደ አፈር የሚለው አምላካዊ ትዕዛዝ ይፈፀም ዘንድ ታመው ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ77 ዓመታቸው በ7/4/2013 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ለአባ ጂኖ አስክሬን ነገ ከጧቱ 3:00 ሰዓት ጀምሮ በሶዶ ሁለ ገብ ዋናው ስታዲየም አሸኛኘት ይደረጋል፡፡ በነገው ዕለትም ራሳቸው ባዘጋጁትና በተመኙት በተናዘዙት መሠረት በዋጃ ኪዳነ ምህረት የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸው ይፈጸማል፡፡