ዳሞታ የቴክኖሎጂ እና ኢንቨስትመንት ባንክ በምስረታ ላይ ነው
ኅዳር 18 2013 ዓ.ም
ዳሞታ የቴክኖሎጂና ኢንቨስትመንት ባንክ አክሲዮን ማኅበር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የምስረታ ፈቃድ በመውሰድ በምስረታ ላይ መሆኑን አስታወቀ። በምስረታ ላይ የሚገኘው ዳሞታ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ዓላማና ትኩረት አድርጎ የተነሳው ዘመናዊ የፋይናንስ አገልግሎት ለመስጠት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። ባንኩ በትኩረት የሚሠራባቸው ዘርፎች የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመለየት እና አዋጭ የሥራ ፈጠራና የንግድ ሐሳብ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አስታቋል።
ለዚህም የሥራ ፈጣሪዎች ልማትና ፋይናንስ(Entrepreneurs Developmenet and Finance) የሥራ ክፍል መቋቋም፣ ለአገር ሊጠቅሙ የሚችሉ ግለሰቦችን እና ድርጅቶችን የብድር አቅርቦት እንዳገኙ እንደሚደርግ የባንኩ ዋና ሰብሳቢ ኤሊያስ ሎሃ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ለዚህም ባንኩ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ የተሻለ የንግድ ሐሳብ ለሚቀርቡ ሥራ ፈጣሪዎች በዓመት ከሚገኘው ገቢ አምስት በመቶ ያክሉን በመመደብ የፋይናንስ አቅርቦት እንደሚሠራ ዋና ሰብሳቢው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የገጠሩ ማኅበረሰብ ክፍል የባንክ አገልግሎት እንዲያገኝ፣ በንግድ ሥራዎች የተሻለ ተሳትፎ እንዲያደርግ ማገዝ እና የኑሮ ለውጥ እንዲያመጣ የጋራ አወቃቀሮችን በመከተል በፋይናንስ ገበያው ላይ ለውጥ ለማምጣት የሚሠራ ባንክ እንደሚሆን ተመላክቷል። የገጠሩን ማኅበረሰብ ኑሮ ለማቅለልና የባንክ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራ ተጠቁሟል።
በምስረታ ላይ የሚገኘው ዳሞታ ባንክ ወደ ባንክ ኢንዱስትሪው ለመቀላቀል ለኹለት ዓመት ሰፊ ጥናት ማድረጉን ዋና ሰብሳቢው ገልጸዋል። በኹለት ዓመት ጥናት በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የግልና የመንግሥት ባንኮች አሁን ላይ ያልደረሱበትን የሥራ ዘርፍና የማኅበረሰብ ክፍል መለየቱ ዋና ሰብሳቢው አስታውሰዋል። በተደረገው ጥናት አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት ባንኮች ያልደረሱበትን ከፍተት መለየት እንደተቻለም ተመላክቷል።
በዚህም አሁን ሥራ ላይ ያሉት ባንኮች ከፍተኛውን ጥቅምና አገልገሎት እየሰጡ የሚገኙት ለራሳቸውና ለባለሀብቱ ብቻ መሆኑን ለመታዘብ በጥናቱ መታዘብ እንደተቻለ ተጠቁሟል።
በምስረታ ላይ የሚገኘው ዳሞታ ባንክ መግዛት የሚቻለው የአንድ አክሲዎን ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ነው ተብሏል። አንድ ባለ አክሲዎን ዝቅተኛ መግዛት የሚችለው የአክሲዎን ብዛት 50 ሲሆን ይህም 50 ሺሕ ብር ማለት ነው። በግለሰብ ወይም በድርጅት መግዛት የሚቻለው ከፍተኛ የአክሲዎን መጠን አንድ ሚሊዮን ብር እንደሆነ ተጠቅሷል። የአክሲዎን ሽያጩ በ17 የኢትዮጵያ በንኮች ዝግ አካቀውንት ተከፍቶ በሽያጭ ላይ መሆኑ ተመላክቷል።
የባንኩ መስራቾች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እስከ ምክትል ገዥ ድረስ ያገለገሉ ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች፣ የባንክ እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መሆናቸውን ዋና ሰብሳቢው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። የባንኩ ዋና ሰብሳቢ ኤልያስ ሎሃ ሲሆኑ ምክትል ሰብሳቢው ያቆብ አልታየ ናቸው። እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህሩ አሰፋ ሀ/ማሪያም(ፕ/ር) አባል መሆናቸው ታውቋል።
ባንኩ የቴክኖሎጅ እና የኢንቨስትመንት ባንክ እንደመሆኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓት ለመከወን ከወዲሁ ባለሙዎችን ወደ ኬኒያ ልኮ ጥናት እያሥጠና መሆኑ ተጠቁሟል።
ኢንቨስትመንት ባንክ የንግድ ተቋማትን እና ገንዘብ ይዘው በምን የንግድ ዘርፍ እንደሚሰማሩ የጠራ ሐሳብ የሌላቸውን አካላት አቀራርቦ በማገናኘት የተሻለ የንግድ ግንኙነት እንዲሁም ኹለቱንም አካላት በጥቅም ማስተሳሰር አንደኛው ሥራው እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ተቋማትን ያሉበትን ደረጃ በማየትም የማማከር እና ሌሎች አማራጮችንም እንዲከተሉ የሚመክር እንደሆነም ይታወቃል።
ኢንቨስትመንት ባንክ በተለያዩ ንግድ ዘርፎች ለሚሰማሩ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ በዘርፉ የሠለጠኑ እና ጥልቅ እውቀት ያላቸውን ሰዎችን በማሳተፍ ለተገልጋዮች ነባራዊውን የአገርም ሆነ የዓለም ዐቀፍ የንግድ እንቅስቃሴን ታሳቢ እያደረጉ ሰፊ ምክር በመስጠት፣ የንግድ እንቅስቃሴውን በማየት ወደ ፊት ከመሔዳቸው አስቀድሞ ሌላ አማራጮችን እንዲወስዱም ምክር እንደሚለግስ እና ካፒታል የመፍጠር ሥራም እንደሚሠራ ለማወቅ ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን 16 የግልና ኹለት የመንግሥት በአጠቃላይ 18 ባንኮች በሥራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከ17 በላይ ተጨማሪ ባንኮችም ለመመስረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቅድመ ምዝገባ ፍቃድን ጠይቀዋል ። ከነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ፍቃዱን አግኝተው በምስረታ ሂደት ላይ ይገኛሉ። (ምንጭ፡- አዲስ ማለዳ፡ ኅዳር 12 2013 ዓ.ም)