ዩኒቨርሲቲውን ብልፅግና የሚባለው “ቡዳ” በላው?
ኅዳር 7 2013ዓ.ም
ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ በህብረተሰባችን የአስተሳሰብ መዳበር አንዲሁም የስነ-ምግባር ልቀት ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና መጫወት እና ዕድሜ ጠገብ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የደረሱበት ለመድረስ በትጋት እንሰራለን የሚለውን ዩኒቨርሲቲ ብልፅግና የሚባለው ቡዳ በላው፤ እንደ አንድ የክርስትና እምነት አስተምህሮ (የእምነት ተቋሙን መጥራት አያስፈልግም) ቡዳ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ዛር ሲሆን እንደ ልክፍት የሚይዝ ፣ ከውጪ ወደ ውስጥ ወደ ሌሎች የሚሄድና በሌሎች ላይ የሚያርፍ መንፈስ ነው፡፡
የቡዳው የብልፅጋናና የሕወሀት ያለመስማማት “አዝሃለሁ” “አታዘኝም” አይደለም፤ ፕሬዝዳንቱ እንዳለውም “የህግ የበላይነትን ማስከበርና ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ማስጠበቅ” ጋርም አይያያዝም፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ቁንጮ ላይ ላለ ሰው በህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝምና በአሃዳዊ ርዕዮት መካካል ያለውን ግብግብ ከመካድ የመነጨ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ካልሆነ በስተቀር፡፡
ዩኒቨርሲቲው የ2013ዓ.ም የስራ ዘመን የትኩረት መስኮችን በተራ ቁጥር ከአንድ እስከ ዘጠኝ በአደባባይ ከገለፀ በኋላ ቅልጥም እንዳገኙ ተንባዮች አለቦታ እንደ ሮኬት መተኮሱን ምን አመጣው? በስምንቱ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ሊግ ውስጥ ለመግባት ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትኩረት አቅጣጫ ማተኮር ሲገባው ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ለመቆም መቋመጥ ምን የሚሉት ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ነው?
አንድ ዩኒቨርሲቲ ተልዕኮ ሲኖረው ያንን ለማስፈፀም ዕውቀት የሚባል ሰይፍ አለው፤ ዕዉቀት ደግሞ የብዙ ዓመታት ልፋትና የማሰብ ዉጤት ነው፤ የተቋማቱ መምህራንም ያን ዕውቀት ታጥቀው ትዉልድ ይቀርፃሉ፤ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ከወታደሩ ጎን መቆም የተቀጠሩበትና የሚገመገሙበት አይደለም፤ መምህራኑ ጥሪያቸው ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት ዕዉቀት ማስጨበጥ፣ የመነሻና የመጨረሻ ግባቸው ነው፡፡ አለመታደል ሆኖ በፖለቲካው የሥልጣን ወንበር ላይ የወጣ ሁሉ ከመቅፅበት ያለ ሀፍረት የሁሉ ነገር አዋቂ መምሰል ያምረዋል፤ አዋቂ አማካሪም አይፈልግም፤ አላዋቂ ፖለቲከኛ አለማወቁ እየታወሰው የእዉቀት ባለሞያዎችን በፖለቲካው ሥልጣን ለመበቀል ይፈልጋል፤ በህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝምና በአሃዳዊ ርዕዮት መካካል ያለውን የብልፅግናና የሕወሃት ግጭት “የህግ የበላይነትን ማስከበር እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓት ማስጠበቅ” በሚባል የተንሸዋረረ የዕይታ አዙሪት ማድበስበስ በማያውቁት ጉዳይ አዋቂ መስሎ መናገር ነው፤ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ውሸትም አለበት፤ ደግሞም አውቃለሁ የሚለውን ሁሉ እንዲሁ በየዋህነት መቀበል ቂልነት ነው፡፡
የብልፅግናው አመራር ስልጣን የሚመራው በግል ጥቅም ነው፤ የዕውቀት ባለሞያው መምህሩ የሚመራው በዕውነት ነው፤ ጉልበት ዕዉቀት አይሆንም፤ ለዚህም ነው ጉልበት የአራዊት መተዳደሪያ የሆነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው የአዋቂዎች የዕዉቀት ቤት ይሁን፤ ከብልፅጋናው ቁንጮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የአላዋቂዎች ዛር አይውረሰው፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም ካማረህም ሩቅ አታማትር ለሥልጠና ብላቴ ቅርብ አለልህ!