ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመራሮችና ካድሬዎች – ህዝብ ይጠይቃል እንጂ አይለምንም!!!

መድህን ማርጮ (ዶ/ር) መስከረም 23 2016ዓ.ም

የይግባኝ ሰሚ ጠ/ፍ/ቤት ጉዳይ የክልሉን ዕድሜ ሊያሳጥረው እንደሚችል ዛሬም ዳግም ልንገራችሁ፡፡ ይህንን ህዝብ ይጠይቃል እንጂ አይለምንም፡፡

የክልል ይግባኝ ሰሚ ጠ/ፍ/ቤት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ እየሰራ አይደለም፡፡ጠ/ፍ/ቤቱ የተቋረጠውን ሥራ እንዲሁም ወላይታ የሚገኘው ምድብ ችሎት በቦታው ማስቻል እንዲቀጥል ተደርጓል በሚል ከሁለት ሳምንት በፊት የተናፈሰው ወሬ የህዝብን ቁጣ ለማስቀየስ የተለቀቀ ማደናገሪያ እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ በሌላ አገላለጽ ለአሁን የፍትህ ሥራ መስተጓጎል ብቻ ሳይሆን ድሀው ህዝብ ለፍትህ ይግባኝ ሰሚ ጠ/ፍ/ቤት ፍለጋ ከወላይታ፤ ዲላ፤ አ/ምንጭ ጂንካ ወደ ጎፋ/ሳውላ ለመንገላታት የመዳረጉ ዕዳ ቀረ ወይሰ አልቀረም የሚለው አሁን አልለየለትም ማለት ነው፡፡ ይህ እጅግ አደገኛ አዝማሚያ ነው፡፡

አንግዲህ የአዲሱ ክልል አመራር በማወቅ ይሁን አለማወቅ ክልሉን ገና ከምስረታው ለመናድ እየሰራ ለመሆኑ ይህ ራሱን የቻለ አመላካች ነው፡፡ ባለፈው ባቀረብኳቸው ጽሁፎች መዋቅር የሚከለሰው ለተሸለ አፈጻጸምና ተደራሽነት እንደሆነና በክልሉ ፍትህ ለደሀው ተደራሽ ለማድረግ ከሳውላ በተጨማሪ በክልሉ ዞኖች ቢያንስ ወላይታ፤ አ/ምንጭ፤ ዲላ እና ጂንካ ተጨማሪ ጠ/ፍ/ቤት ምድብ ችሎቶች መደራጀት እንዳለባቸውና ይህም ጊዜ ሊሰጠው እንደማይገባው ጠቁሜ ነበር፡፡ ማንም ሊሰማው አልፈቀደም፡፡

እንግዲህ አመራሩ በልግስና የሚቀርብለት ምሁራዊ ምክርና የመፍትሔ ሀሳብ የማይሰማ ከሆነ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው ህዝብ ለመብቱ እንዲንቀሳቀስ መምከር ግዴታችን ይሆናል፡፡ ምንም ምክንያት በሌለበትና ተጨማሪ ምድብ ችሎቶች መደራጀት ሲኖርበት ከወላይታ ጠ/ፍርድ ቤት ምድብ ችሎት የሚነሳ ከሆነ የወላይታ ህዝብ ዛሬ ነገ ሳይል ይህንን ክልል አፍርሶ መከራውን ለማሳጠር ለትግል ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በተላይ በአከባቢው ያላችሁ የፍትህ አንገብጋቢነት የበለጠ የምትረዱ የህግ ባለሙያዎች ጠበቆችና ዳኝነት ተግባር ላይ የተሰማችሁት ሀላፊነታችሁ ከሙያዊነት በላይ የሚዘል መሆኑን ላሳስባችሁ እወዳለሁ፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአቶ ጥላሁን ከቢኔና ለአጠቃላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አመራር ምናልባትም የመጨረሻ ምክሬን አሁንም ለመድገም እወዳለሁ፡፡ ሀሳቡን ብትሰሙ ጥቅሙ ከማንም በላይ ለእናንተው ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ ከ30 በላይ ብሔር አንድ ላይ ባጨቀው የክልል አወቃቀር ተጠቃሚው የወላይታ፤ ጋሞ፤ ጌዲኦ፤ ጎፋ ወዘተ ድሐው ህዝብ ሳይሆን እናንተው ማለትም በህዝቡ ስም በሹመት የተንበሸበሻችሁ የዘመኑ ባለሟሎች ናችሁ፡፡ የህዝቡን በደል ከሆነማ ለአብነት አንድ፤ሁለት እያልኩ እንደሚከተለው መዘርዘር እችላለሁ፡፡

1. ዛሬ የወላይታ፤ጋሞ፤ጌዲኦ፤ጎፋ… ህዝብ በአንድ ክልል በመጨፍለቁ ምክንያት ትናንት ከእነሱ ጋር በህዝብ ብዛትና ዓመታዊ በጀቱ ተቀራራቢ ሆኖ ደ/ብ/ብ/ህ/ ክልል ሥር የነበረው ሲዳማ ራሱን ችሎ ክልል በመመስረት ለ2016 ዓ/ም በጀት ዓመት ወደ 23 ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ሲበጅት እናንተ አንድ ቅርጫት ውስጥ የወተፋችዋቸው ሶስትና አራት ብሔር ዞኖች ድምር ዓመታዊ በጀት ከዚያ አይስተካከልም፡፡ ይህ ለጆሮ የሚቀፍና የህዝቡን የመልማት ዕድል የሚያቀጭጭ ተጨባጭ ጉዳት ነው፡፡ ከወላይታ ያነሰ ህዝብ ቁጥር ያለው አፋር፤ ጋምቤላ፤ ቤንሻንጉል ጉምዝ፤ ከጋሞ ያነሰ ቁጥር ያለው ጋምቤላ፤ ጉምዝ፤ እንዲሁም ከጌዲኦም ጎፋ ያነሰ ህዝብ ቁጥር ያላቸው ቢያንስ ሁለት የብሔር ክልሎች ሀገሪቱ ውስጥ መኖራቸው እየታወቀ የእኛዎቹ ራሳቸውን በራስ የማስተዳደር ህገ-መንግስታዊ መብት ተነጥቀውና ለየብቻቸው በመሰረቱት ክልል በቋንቋቸው ያለገደብ የመጠቀም መብትና በስማቸው በመሰረቱት ክልል የመጠራት ሉዓላዊ ክብራቸውን ሰውተው ስም፤ ዋና ከተማና ክብር-አልባ አደረጃጀት ሥር ተጠርንፈው ነው በህዝቦቹ ክብርና ጥቅም ኪሳራ /Expense/ የተዋቀረ ደቡብ ኢትዮጵያ የሚል ክልል የተደራጀው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ከበርካታ ጉዳቶች ጥቂቶቹ እንደሆነ ይነገረን ካላችሁ ይሔውና ስሙት፡፡ በተቃራኒው ግን ስለእናንተም መነገር ካለበት እናንተ በሕዝቡ ኪሳራ በእልፍ ሹመት ተለቃለቃችሁ፡፡ ከርዕሰ-መስተዳደርና አፌ-ጉባዔዎች በተጨማሪ አንድ ም/ር/መስተዳደር፤ ስድስት በም/ር/መስተዳደር ማዕረግ ደረጃ ሹማምንት፤ 23 የቢሮ ሀላፊዎች፤25 ተጨማሪ የቢሮ ሀላፊ ማዕረግ ደረጃ ሹማምንት እና 108 ም/ቢሮ ሀላፊዎች ሆናችሁ ተንበሸበሻችሁ፡፡ መቼም የእናንተ የሹማምንት መዝባሪና ያለቅጥ የተጋነነ ቅንጡ የጥቅማጥቅም ጥቅል (package) እና አቀማመር ለህዝብ በይፋ ባይነገርም ሙሉ በሙሉ ከህዝብ የተሰወረም አይደለም፡፡ አንድ የክልል ቢሮ ሀላፊ ከደሞዙ ውጭ በወር ለቤት ኪራይ ብቻ 18000 ብር፤የኪስ ገንዘብ ለግብዣ እየተባለ በየቀኑ እስከ 2000 ብር (በወር ባይሰላ የሻላል)፤ለሞባል ቀፎ መግዣ ተብሎ በዓመት 25000 ብር፤ አልጋ ባለ አራት ኮኮብ ተፈልጎ የሚተኛበት እንዲሁም ያልተገደበ (unlimited) የስልክ ወጭ የሚወራረድበት ልቅ ቀመር ሥር ከዚህ ሁሉ ወፌ-ሰማይ ሹማምንት ምን ገንዘብ ተርፎ ነው አዲስ ለተዋቀረ ክልል ድሐ ህዝብ ጠብ የሚል ነገር የሚሰራለት? ለዚያውም የክልሉ ቢሮዎች ስድስት የተለየየ ከተማ ላይ እንደ ጸበል ተረጭተው፡፡ መልሱን እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡

በአጭሩ አዲስ የተዋቀረው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አወቃቀሩ ከመነሻውም በውስጡ ላሉት በተላይም በርከት ያለ ቁጥር ላላቸው እንደ ወላይታ፤ ጋሞ፤ ጌዲኦና ጎፋ ብሔሮች፤ (በተላይም ለወላይታ) እጅግ አክሳሪ መሆኑን በደንብ እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ወላይታን ከባስኬቶ፤ ኮሬ፤ኮንሶ ወዘተ ዕኩል በዞን ደረጃ ማደራጀት ጉዳት ብቻ ሳይሆን አደረጃጀታዊ/መዋቅራዊ የሆነ ሰው-ሰራሽ መቅሰፍት መሆኑን በግልጽ እያወቅን ቢያንስ ጉዳቱን ለመቀነስ የሚረዱ ምክሮቹን አቧራው ሲሰክን ለመጠቆም በይደር አቆይተን ነበር፡፡

ይሁን እንጂ እንደ አያያዛችሁ ከሆነ የፖሊሲ ምክርም ሆነ አስተያየት እንደማትሰሙ ወይም እንደማትረዱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎት ጉዳይ አያያዛችሁ ዓይነትኛ ማሳያ ይመስላል፡፡ ሆኖም ዛሬም ምክሬን ለመጨረሻ ጊዜ ልደገመው ወደድኩት፡፡ በህዝብ ፍትህ ላይ መቀለዱ በፍጥነት መቆም ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ሲባል ድሐ ህዝብ ለፍትህ ሲል የሚያወጣው አላሰፈላጊ እንግልትና ወጭ (cost of justice) ለማስቀረት ቀጥሎ የቀረቡት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ይፈልጋሉ፡፡

1. ከነሐሴ 19 /2015 ጀምሮ ያለአግባብ ተቋርጦ የቆየውና ከቦታው ይነሳል የሚል ጭምጭምታ እየተናፈሰ ያለው የወላታው ጠ/ፍ/ርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ምድብ ችሎት በአስቸኳ ሥራውን እንዲቀጥል እንዲደረግ

2. ሌሎች ጠ/ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ምድብ ችሎቶች በዲላ፤ አ/ምንጭና ጂንካ እንዲደራጁ እንዲደረግ

3. እነዚህን አዳዲስ ምድብ ችሎቶቹን በሰው ሀይልና ሎጂስቲክስ ማደራጀት ጊዜ ይፈጃል ከተባለም ለጊዜው በተመረጡት ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የይግባኝ ሰሚ ችሎት ውክልና በመስጠት ለደሀው ህዝብ ፍትህ with low and affordable cost of justice እንዲዳረስ እንድደረግ እንደ አንድ የክልሉ የተማረ ዜጋ የህግ ግንዛቤ በሚጎለው ሰፊውና ደሀው የክልሉ ማህበረሰብ ስም አጥብቄ እጠይቃችሁሃለሁ፡፡ የህዝብ ጥያቄ የማትሰሙ ከሆ ግን በማወቅም ሆነ አላማወቅ ክልሉን በፍጥነት ለማፍረስ እየሰራችሁ መሆኑን ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡

የክልሉን ጠቅላይ ፍ/ቤት ምድብ ችሎት ከወላይታ ሶዶ ማንሳት ህጋዊና ምክንያታዊ አይደለም!!!

ዶ/ር መድህን ማርጮ (ነሐሴ 23 2015ዓም)

መዋቅር ተከልሶ ሲዋቀር ፊት ከነበረው የተሻለ ፍትሐዊነት: ተደራሽነትና ቅልጥፍና ማረጋገጥ የግድ ነው:: አዲስ የተዋቀረው ደቡብ ቢሮዎችን 6 ቦታ ማዝረክረኩ ክልሉን ለከፍተኛ የበጀት ብክነት ተገልጋዩን ለከባድ እንግልት የሚዳርግ በመሆኑ ቶሎ መፍትሄ ካልታሰበ የክልሉ ዕድሜ ከ5 ዓመት በታች እንደሚሆንና አንድ ወይም ሁለት ብሄር ከዚህ ክልል ማዕቀፍ ውስጥ በብጥብጥም ቢሆን ተነጥሎ መውጣት እንደማይቀር ከግምት በላይ መናገር ይቻላል::

ከፍ ያለ ህዝብ ቁጥር ያለው ብሄር በአንድነቱ ምክንያት የሚደርስበት የበጀት በደል እንደተጠበቀ ሆኖ መዋቅሩ ተጨማሪ በደሎች ማበራከት የለበትም:: የክልል ቢሮዎች እንደቅርጫ አሥር ቦታ መርጨት ሳይሆን ለማህበረሰብ ቅርብ መሆን ሚገባቸው እንደ ፍርድ ቤት ያሉት ቁልፍ ሰክተሮች ቢቻል በየዞኖቹ ማዕከላት ካልሆነም በተመረጡ ማዕከላት ማደራጀት አፋጣኝ ማሻሻያ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው::

በዚህ ረገድ ከፍትህ ጉዳይ አንገብጋቢነት አንፃር ነባሩን የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት ማሥተባበሪያ ከሶዶ ማንሳት ሳይሆን ተመሳሳይ ማሥተባበሪያዎችን ጅንካ አ/ምንጭና ዲላ ማደራጀት አንገብጋቢ ነው:: እናም ከሥር ጠበቃ ተከተል ላቤና የወላይታ ሶዶን ጠ/ፍ/ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት እንዲነሳ መታዘዙን አስመልክቶ ያቀረበው ሐሳብ የሶዶን በማንሳት ሳይሆን በዚህ መልክ ታርሞ ምላሽ ማግኘት ይገበዋል ባይ ነኝ:: በክልሉ ውስጥ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ሰብዕዊ አደረጃጀት እጅግ ደካማ በመሆኑና ክፍተኛ ፍ/ቤቶች ከሥር ወረዳ ፍ/ቤቶች ጋር ያለው ኢ-መደበኛ ቅርርብ ፍትህ ላይ በሚያደርሰው አሉታዊ ሚና ምክንያት ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት የሚመጣ ይግባኝ ብዛት እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ የጠ/ፍ/ቤት ተደራሽነት ከህዝብ ማራቅ አደጋው ከባድ ነው:: የተከተል ፅሁፍ ሙሉ ሐሳብ ቀጥሎ ቀርቧልና አንብቡት::

ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል| በወላይታ ሶዶ ከተማ ላለፉት 15- ዓመታት አገ/ት ሲሠጥ የነበረ የክልሉን ጠቅላይ ፍ/ቤት ምድብ ችሎት ማንሳት ህጋዊና ምክንያታዊ ባለመሆኑ እንዲታረም፤

በፈረሰው ደ/ብ/ብ/ክ መንግስት በምክር ቤት ተወሰኖ ” በወላይታ ሶዶ እና ሆሳና ከተማ” የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ምድብ ችሎቶች ተቋቋመው ላለፉት 15 ዓመታት አገልግሎት ሲሠጡ የነበሩ መሆኑ ይታወቃል።። ይሁን እንጂ በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኘውን ምድብ ችሎት ያለምክር ቤት ውሳኔ ለማንሳት ትዕዛዝ መሰጠቱን መዝገብ ለመክፈት በሄድኩበት ጊዜ ለማረጋገጥ ችያለሁ። በመሆኑም ይህንን የአዲሱን ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትዕዛዝን በሚከተሉት ህጋዊ ምክንያቶች እቃወማለሁ!

1. ይህ ምድብ ችሎት እና በሆሳና ከተማ የሚገኘው በሸድሞው ደ/ብ/ብ/ክ መንግስት በምክር ቤት ተወሰኖ ተቋቋመው ላለፉት 15 ዓመታት አገልግሎት ሲሠጥ የነበረ ሲሆን ካቢኔ አባላትን አሟልቶ ባልሾመው አዲሱ ክልል እንዲነሳ ትዕዛዝ መሰጠቱ ህገ መንግስታዊ አይደለም። [ ምክንያቱም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህገ መንግስት በዚህ አዲሱ ክልል መመሪዎችና ደንቦች እስኪወጡ ድረስ የነባሩ ክልል መመሪዎች፣ደንቦችና የም/ቤት ውሳኔዎች ተፈፃሚነት እንዳለቸው ያስቀምጣል በግልፅ ያስቀምጣል። ] በመሆኑም በም/ቤት የተመሠረተውን ምድብ ችሎት ያለምክር ቤት ውሳኔ የማፍረስ ሥልጣን ለአሥፈፃሚ አካላት የላቸውም!

2. ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መሥራች ፕሮጀክት ጽ/ቤት በሐዋሳ ከተማ ላይ የተቀመጡ የቀደመውን ክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዋና መ/ቤትን እና ሌሎች የፍትህ ተቋማት ወደ ጎፋ ዞን እንዲሆዱ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል እንጂ በወላይታ ሶዶ ከተማ ያለውን ምድብ ችሎት እንዲነሳ ባለመሆኑ፣

3. ምድብ ችሎት በተመሳሳይ ሁኔታ በነባሩ ክልል በሆሳና ከተማ የነበሩ ሲሆን የሆሳና ከተማ ምድብ ችሎት ማዕከላዊ ክልል ሲደራጅ እንዲነሳ ባልተደረገበት ሁኔታ የወላይታ ሶዶ ምድብ ችሎት እንዲነሳ ትፅዛዝ መስጠቱ ተገባነት የሌለው ስለሆነ፣

4. አዲስ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለህዝቡና ለዜጎች ከፈረሰው ደ/ብ/ብ/ክልል በተሻለ ሁኔታ ተደራሽ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ የተፋጠነና ውጤታማ ፍትህ የማድረስ ህገ መንግስታዊ ሃላፊነት [በፌዴራልና በክልሉ ህገ መንግስት] የተጣለበት በመሆኑ ለ15-ዓመታት ህብረተሰቡ በምድብ ችሎቱ የሚያገኘውን አገልግሎት ለማቋረጥ ትፅዛዝ መሰጠቱ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት የሚጎዳ ስለሆነ፣

5. በአዲሱ ክልል ከሚኖረው ተገልጋይ ከ75% በላይ የሚሆነው ከዚህ በፊት በምድብ ችሎቱ የሚጠቀም በመሆኑ ለተጨማሪ እንግልትና ስቃይ የሚዳርግ በመሆኑ መንግስት በፍትህ ጥማት ለከፍተኛ እንግልትና ስቃይ በሚጋለጡ አቅመ ደካማ ዜጎች ስም እጠይቃለሁ፡፡