በወንድማማቾች መሀከል በሚደረግ ጦርነት አሸናፊ ኖሮ አያውቅም!!
ጥቅምት 26 2013ዓ.ም
እንደ ሀገር ተመልሰን ወደ ደረግ ግዜው ወንድም ወንድሙን እንደ ጠላት ወደሚገድልበት ዘግናኝ የእርስ በርስ ጦርነት (Civil War) መመለሳችን እጅግ አሳዛኝ የሆነ ነገር ነው:: አሁን መሬት ላይ ባለ እውነታ የህወሓቱ ቡድን ላለፉት ሁለትና ሶስት አመት ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ረዘም ላለ ግዜ ለአሁኑ eventuality ሲዘጋጅ እንደነበር መገመት አይከብድም:: በዚህ ሁኔታ ደግሞ የፌዴራሉ የመከላከያ ሰራዊት ሀይል የጀመረው ኦፐሬሽን በአጭር ግዜ ይጠናቀቃል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው የሚሆነው:: ዛሬ አመሻሽ ላይ በጀርመን ድምፅ ራድዮ የአማርኛው የቀጥታ ስርጭት (DW Amharic live streaming) እንደተዘገበው የሰሜን ዕዝ ከባባድ የጦር መሳሪያዎች በትህነጉ ልዩ ሀይል ጥበቃ ስር እንደሆነ መገለፁ የሀይል ሚዛኑ በአንድ ወገን ብቻ የመሆኑን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል:: በሌላ አገላለፅ ይህ ጦርነት የተራዘመ የርስ በርስ ግጭት (protracted civil war) መልክ የመያዝ እድሉ ሰፊ ነው::
በየትኛውም በኢትዮጵያ ቦታ ያለች ያልተረጋጋ የውስጥ ፖለቲካ ያላት ሀገር ውስጥ እንደዚህ አይነት ግጭቶች የመፈጠሩ ነገር የግዜ ጉዳይ እንጂ የማይቀር እውነታ ነው:: በተለይም ደግሞ የማዕከላዊ መንግስት ስልጣንን በሽግግር ፖለቲካ በያዘ ቡድንና ቀድሞ የኸንኑ የማዕከላዊ መንግስት ስልጣን ይዞ የነበረ ግን በሽግግር ወቅት የስልጣን መጋራት ስምምነት በሌለበት ሁኔታ ሙሉ አቅሙን ይዞ ወደ ዳር ፖለቲካ (pheriphery politics) ያፈገፈገ ቡድን መሀከል በdialogue መግባባትና compromise ላይ መድረስ ባልተቻለበትና ፍቃደኝነቱም በሌለበት እንደዚህ አይነት ሀገራዊ እውነታ አሁን የተገባበት በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት (armed conflict) የ”መች” ጉዳይ እንጂ የ”ይሆን ይሆን” ጉዳይ አይደለም::
ከእኛ በተመሳሳይ የውስጥ ፖለቲካ ጎዳና የሄዱትን ሊቢያኖች ያየን እንደሆነ በመጀመሪያ በታጠቁ ሀይሎች መሀከል ብቻ የነበረ ግጭት ግጭቱ የተራዘመ ገፅታ እየያዘ በሄደ ቁጥር ሰላማዊ ህዝብ የጦርነቱ ሰላባ እየሆነ በመሄዱ ወደተለያዩ ቡድኖች የሚወግኑ የጦር ሰራዊቱ መሪዎች መሀከል መከፋፈል እየተፈጠረ ሄዶ የተለያዩ በርካታ ተመጣጣኝ የሀይል ሚዛን ያላቸው የጦር አበጋዞች ቡድኖች መፈጠር አይቀሬ ሆኖ ላለፉት ዘጠኝ አመታት በእርስ በርስ ጦርነት ደቅቃ failed state ልትሆን ችላለች:: የኛው አሁን የተገባበት ግጭት ደግሞ በሰሜኑ ክፍል ብቻ ተወስኖ ይቀራል ብሎ ማለት የጦርነትን (በተለይም ደግሞ እንደዚህ በሁለት የፖለቲካ ቡድኖች የስልጣን ሽኩቻ መነሻነት ተጀምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ጭምር ተሳታፊ ወዳደረገ ሰፋ ወዳለ የእርስ በርስ ግጭት የመሸጋገር ባህርይ ያላቸውን ግጭቶች) ፀባይ ካለመረዳት የሚመነጭ የተሳሳተ ስሌት ውጤት ነው የሚሆነው::
ስለዚህ በሀገሪቱ ቀጣይ ህልውና እና በዚህ ትርጉም የለሽ ጦርነት በሁሉም በኩል የሚሞቱ ኢትዮጵያዊያን ነፍስ ጉዳይ ያገባኛል ሀላፊነት አለብኝ ብሎ የሚያምኑ የሀገር ሽማግሌዎች: የሀይማኖት ተቋማትም ሆነ የሲቪል ተቋማት መሪዎች እርቅ የሚወርድበትንና ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው:: የሀገርን ቀጣይነትና የዜጎቿን ደህንነት ለማረጋገጥ እና እንደሰደድ እሳት በመላው ሀገሪቱ ሊፋፋም የሚችል የእርስ በርስ ጦርነት (civil war) ከጅምሩ ለማስቀረት ለሚደረግ ውይይት መቼም ሊረፍድ አይችልም::