በዎላይታ ክልል ጥያቄ ምክንያት ታስረው ማረሚያ ከሚገኙ ታጋዮች የተላለፈ መልዕክት!!
ጥቅምት 10 2013ዓ.ም
መላው የዎላይታ ህዝብ የአገር ሽማግሌዎች፣የሀይማኖት መሪዎች፣የላጋዎች፣የመንግስትሠራተኞች፣አመራሮች፣መምህራን፣የንግድ ማህበረሰብ፣ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራርና አባላት፣ የሴቶች ማህበራት ፣ምሁራን፣ዲያስፖራ ማህበረሰብ እና ሌሎች ሕዝባዊ ተቋማት የወላይታን ህዝብ በክልል የመደራጀት ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በመምራትና በማታገላችን ምክንያት ኢ-ህገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ወደ ማረሚያ ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ በየ እምነት ተቋማት ፆምና ፀሎት በማድረግና በአካል እስከ ዎላይታ ሶዶ ማረሚያ በመምጣት ስላበረታታችሁን እንዲሁም በተለያየ መልኩ ከአጠገባችን መሆናችሁን ስላረጋገጣችሁ ያለንን አክብሮትና ልባዊ ምስጋና በመላው ታጋዮቻችን ስም ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።
በሌላ በኩል ሕዝበ እስራኤል የተስፋይቱን ምድር ለመውረስ በሚያደርገው ጉዞ እንቅፋት በገጠመ ቁጥር ሙሴ ላይ በማማረር የግብጽን ሽንኩርት የሚመኙ ሰዎች እንደነበሩ ሁሉ፤ በአሜሪካ የጥቁሮች የነፃነት ትግል በሚደረግበት ወቅት ከጨቋኝ ነጮች ጋር በመተባበር የለመድነው የበታችነት ኑሯችን ይሻለናል ብለው የሚሞግቱ የጭቆና ገፈት ቀማሾች እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም መዋቅራዊ ጭቆና ለመገርሰስ ሁለንተናዊ ነጻነት ለመጎናፀፍ በሚደርገው አጭርና መራራ ትግል ከህዝቡ ፍላጎትና አስተሳሰብ በተቃራኒ ቆሞ የነፃነት ጉዟችንን ለማርዘም የሚተጉ የውስጥም የውጭም ጎታች ኃይሎች መኖራቸውን መላው ሕዝብ የተገነዘበው ስለሆነ በቀሪ አጭር ጊዜያት ከክፉ ሀሳብና ድርጊታችሁ ቶሎ ተጸጽታችሁ በመመለስ በሕዝባዊ ትግሉ እንድትቀላቀሉ በድጋሚ ጥሪ እናቀርባለን።
በመጨረሻም ሕዝባችን ባደረገው ጠንካራ ተጋድሎ ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሶ የነበረው በክልል የመደራጀት ጥያቄያችን በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርቶ በተደርገ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ምክንያት የዘገየው ህገ መንግስታዊ ጥያቄያችን ምላሽ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘቱ ስለማይቀር ሕዝባችን የተለመደውን ሰላማዊ ትግል አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ትግላችን አጭርና መራራ ነው!!
(ምንጭ፡- ወተ)