ዶ/ር አብይ ከካድሬ አሉባልታ ይልቅ የወላይታን ሕዝብ ማዳመጥ ያዋጣዋል!
መስከረም 04 2012ዓ.ም
የወላይታ ሕዝብ በነፃነት ካልኖረ፣ የመሰለውን ሐሳብ ካላራመደ፣ የሚፈልገውን በነፃነት ካልመረጠ፣ በአመለካከቱ ምክንያት የሚደበደብ፣ የሚታሰርና የሚንገላታ ከሆነ፣ ከሥራና ከመኖሪያ ቀዬው ከተፈናቀለ እሪታውና ጩኸቱ ይቀጥላል፡፡ የወላይታ ሕዝብ በመንግሥት ፖሊሲዎችና ሕጎች ዝግጅቶች ላይ በቀጥታም ሆነ በውክልና ተሳታፊ ካልሆነ፣ በሥልጣን የሚባልግ ሹማምንት የሚፈነጩበት ከሆነ፣ በህግ አግባብ ካልተስተናገደ፣ በክልል የመደራጀት መብቱ ከተገደበ፣ በገዛ አገሩ የበይ ተመልካች መሆኑ ከቀጠለ ምሬቱና ጩኸቱ የትም ድረስ ይሰማል፡፡
የዶ/ር አብይ መንግስት ቆም ብሎ አሁንም ማሰብ ያለበት ከሕዝብ በላይ ማንም አለቃ እንደሌለው ነው፤ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ይህንን ማረጋገጥ አለበት፡፡
የወላይታ ሕዝብ የትናንቱን የዛሬውንና ለነገ የታቀደለትን ያውቃል፤ በጥቂት ስልጣን ፈላጊዎችና በደንታ ቢሶች ምክንያት ግን ሲራብና ሲጠማ ለመኖር ህልውናው ሲል ይመክታል፡፡ የወላይታ ህዝብ መብቱ ሲረገጥና ሲንገላታ፣ እንዲሁም ሲታሰርና ሲሰደድ ጩኸት ወደ አመፅ ይለወጣል፤ መንግሥት የወላይታን ሕዝብን እንደ አለቃው መመልከት ትቶ ችላ ሲለው ችግር ይፈጠራል፡፡
የወላይታን ህዝብ ጥቅም ከግላዊ ወይም ከቡድናዊ ጥቅም በላይ ማየት የተሳናቸው ግለሰቦችና ቡድኖች አሳፋሪ ድርጊቶችና የሚፈጽሙ ግለሰቦች ሊወገዙ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሥልጣንና የወላይታን ሕዝብን ሉዓላዊነት ለያይቶ አለመመልከት የወደፊት ሥጋትና አደጋ አለመገንዘብ ነው፡፡ ኩሩ የወላይታ ሕዝብ ይከበር፣ ይደመጥ ሲባል ለአደጋ የሚያጋልጥበት ችግር አይፈጠርበት ማለት ነው፡
ዶ/ር አብይ ካድሬው ሲያሞግሱህ ሆነ ሲሸነግሉ ጊዜያዊ ወዳጅነትና ጥቅማቸውን እያሰሉ ነው፤ በካድሬው ውዳሴና ፈገግታ የተዘናጉ ከሆነ እራስዎን ደጋግመው ይፈትሹ፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ ነውር የሆነ ይመስል የካድሬን አሉባልታ ማድመጥ ይብቃ፤ የወላይታን ሕዝብ ህልውና ከራሳቸው ጥቅም በታች አሳንሰው የሚያዩ በዙሪያዎ የተሰገሰጉ የስልጣን ጥመኞች በተግባራዊ ዕርምጃ ይታረሙ፤ ካልሆነም ይወገዱ፤ የወላይታ ሕዝብ ይደመጥ፡፡
ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ የፖለቲካ ፍትጊያውን በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍትሔ ሰጥቶ አገርን መገንባት ሲገባ፣ በካድሬ አሉባልታ በህዝብ ላይ የሚደርሰው የእልሄኝነት አፀፋ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ መንግሥትዎ የዲሞክራሲ ጉዞ ሰንገው ከያዙት ትልልቅ ማነቆዎች አንዱ የሆነውን የብልፅግና ፓርቲ እና መንግሥት መቀላቀል መካከል ያለውን ልዩነት ያስምርበት፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቱ የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብትን፣ የራስን ክልል የማቋቋም መብትን ጨምሮ፣ ለሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ በእኩልነት ያረጋግጣል። ይህ መብት በወላይታ ተግባራዊ እንዳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያግዱና ሲከላከሉ ቆይተዋል፤ መንግሥትዎ በህግ የበላይነት የሚያምን ከሆነ በተግባር እንደ አስፈፃሚ አካል ያረጋግጡ፤አሻፈረኝ ካሉ ለፍልሚያ ዝግጁ የመሆን ሙሉ መብትዎ የእርሶና የብልፅግና ፓርቲ ድርብ ኃላፊነት ነው፡፡
ኢትዮጵያም የወላይታን ህዝብ መብትና ፍላጎት መጠበቅ ያለባት ለህልውናዋ ስትል ብቻ ነው!!!