ከመጣው ሁሉ ጋር መሞዳሞድ “እናቴን ያገባ ማንም አባቴ ነው” ብሎ የመቀበል የተሸናፊነትና የውርደት ምልክትም ነው!!
መስከረም 03 2013ዓ.ም
ቅንና ቆራጥ የሆኑ የሕዝብ ልጆችን መካድና ከመጣው ጋር መሞዳሞድ “እናቴን ያገባ ማንም አባቴ ነው” ብሎ የመቀበል ያህል ክህዴት ብቻ ሳይሆን የተሸናፊነትና የውርደት ምልክትም ነው፡፡ ሕዝብ የመረጠው አካል በሕዝብ ጥያቄ ከስልጣኑ ይወርዳል ወይም የተሰጠውን የኮንትራት ጊዜ ሲጨርስ ከስልጣኑ ይወርዳል እንጅ ማንም የሕዝብ ሉዓላዊ መብትን በመጋፋት የፈለገውን መሾምና መሻር አይችልም።
በዚህ አግባብ ባሁኑ ጊዜ ወላይታ ውስጥ ከስልጣናቸው የተሻሩት እና በሕግ እየተጠየቁ ያሉት አንድም ጥፋት ፈፀመው እንዳልሆነ ሁሉም የሚያውቀው ሐቅ ነው፤ ይልቁንም የሕዝብ ጥያቄ አንግበው ከሕዝብ ፊት በቅንነትና በቆራጥ አመራርነት ቆመው በመፋለማቸው ነው።
ስለዚህ ኢ-ሕገመንግስታዊ በሆነ አግባብ እና አካሄድ ከስልጣናቸው በጉልበት እንዲነሱ ሲደረግ ሕዝብ ለምን? አይቻልም፤ የማለት ሕጋዊና ሞራላዊ መብት፣ ግዴታና ኃላፊነት አለበት። ካልሆነ ግን ቅን የሕዝብ አገልጋይ በሆኑት ላይ ክህዴት ከመፈፀም ባሻገር በእነርሱና በቤተሰቦቻቸው የእለት እንጀራም ላይ እየፈረድን መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
በሌላ አባባል እነዚህ ቅን እና እውነተኛ የሆኑ የሕዝብ ልጆችና አመራሮች አሁን ላይ የገጠማቸውን ፈተና አብሮ መጋፈጡን ትተንና “እናቴን ያገባ ሁሉ ማንም ቢሆን አባቴ ነው” ብሎ መቀበል ውርዴት፣ ክህዴት እና ተሸናፊነት ከመሆኑ በተጨማሪ ንፁሓንን እየጎተትን ወስደን ከገደል ጫፍ ላይ ከማድረስ ባለፈ ከገደሉም ገፍተን እንደጣልናቸው ሊታውቅ ይገባል። በዚህ ወቅት ማንም እንደጵላጦስ “ከደሙ ንጹህ ነኝ!” ማለት አይችልም፤ የለበትም። የአንዱን መራራ ኮሶ በጋራ መጋት፣ የሁላችን በጋራ መጋት ነው የአንድ በጠንካራነቱ፣ በፅናቱ እና በአንድነቱ የሚታወቅ ሕዝብ መገለጫ።
የክልል ጥያቄና ተያይዞ የተቀጣጠለውን ሰላማዊ የሕዝባዊ ትግል በተመለከተ “እንደ ደረቅ ባህር ዛፍ ቅጠል እሳት” አንድ ጊዜ ሰማይ አድርሰን ወዲያው ዘጭ አድርገን የምንተወው፣ በትንሽ ፈተና ተሸንፈን ቀበቶአችን የምንፈታበት ከሆነ ወይም በትንንሽ ነገር ተታልለን የምናልፈው ከሆነ አሁንም ለሌላው ለዛውም ለቀጣይ ትውልድ ጭምር የሚናወርሰው ትልቁ ውርዴት እና ተሸናፊነት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
የክልል ጉዳይ ከሆነ መቸም የማይቀር የሕዝብ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል። ለዚህም ቢሆን ግን ማንም ያስገኝ ማን ጥያቄያችን ምላሽ ያግኝ ብሎ መተው “በጨው ደንደስ በርበሬ ተወደስ” እንዲሉ እንዲሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ከሕዝብ ጋር የጀመሩት በድሉም ጊዜ ከሕዝብ ጋር ሆነው የደስታ ችቦውን መለኮስ አለባቸው።