ባርነትን እንደ ብኩርና አትንከባከበው!!!

Wolaita Today

 

በክብረአብ ደምሴ

ነሐሴ 25 2012ዓ.ም

ደርግን የተካው ኢህአዴግ ትምህርት ወስዶ የተሻለ ስርዓት ይገነባል ተብሎ ቢጠበቅም፣ በሂደት እሱም የለየለት አምባገነንና አፋኝ ስርዓት ለመሆን ከመብቃቱም በላይ፣ ጭቆና እንዲወገድ፣ እኩልነት እንዲረጋገጥና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመሠረት በሚደረግ ጥረት ሁሉም የወላይታ ተወላጆች ለወላይታ ልማትና ዕድገት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ከመስራት ይልቅ ኢህአዴግ/ዴኢህዴን ጥላቻና አምባገነንነትን የአገዛዙ የአመራር ዘይቤ አድርጓል፤ የኢህአዴግ በኩር ልጅ የሆነው ብልፅግና አካሄድ አሃዳዊ የአምባገነን ስርዓትን ዳግም ለማስፈን እየከወነ ያለው አካሄድና የወላይታን ህዝብ በክልል የመደራጀት መብት መጋፋት ደግሞ ዕዳው የከፋ ነው፡፡

የወላይታን ሕዝብ ጥያቄ በሰላይ ጋጋታና በወታደር ብዛት ማዘግየት ሙከራ እንጂ መጨፍለቅ እንደማይቻል ከኢህአዴግ የ”ወጋጎዳ” ፕሮጀክት በላይ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ድርጊት ሊኖር አይችልም፡፡

በተለይ ደግሞ መንግስት በሚቆጣጠረው የመገናኛ አውታሮች በጥላቻና በሽብር የተሞላ መርዘኛ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ማስተላለፉ የመንግስት ሚዲያ ተቀጣሪዎች ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የስነ ምግባር፣ የሞራል ውድቀት ላይ እንደሚገኙም ጭምር ማሳያ ነው፡፡

የብልፅግና አገዛዙ የወላይታን ሕዝብ በክልል የመደራጀት ፍላጎት በስለላና በጦር ኃይል እጨፈልቃለሁ የሚል አምባገነናዊ አካሄድ የፓርቲውን የቁልቁለት ጉዞ እያፈጠነው ነው፤ ወላይታ ሆነው የክልል ጥያቄ ላይ በተቃርኖ የቆሙ ባርነትን እንደ ብኩርና የሚቆጥሩ የብልፅግና አባላትም ሆነ አመራሩ እየተንደረደሩ እየሄዱበት ያለው የመቀመቅ ጉዞ ወላይታን ሆነ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር አይጠቅም፡፡

በብሔር ወላይታ ሆነው በኢህአዴግ/ዴኢህዴን ሆነ በብልፅግና የነበሩና ያሉ ያልተረዱት ነገር የፖለቲካ ህይወት በቀላሉ መልቀቂያ የሚሰጠው አለመሆኑን ነው፤ አቶ ሐይለማሪያም ደሳለኝ ሆነ ሌሎቹ በሶሻል ሚዲያ የሚብጠለጠሉት ለምንድነው? አቶ ፍሬውስ የሚመሰገነው ለምንድነው? በወላይታ የፖለቲካ ድራማ ገና ያልተወራረዱ በርካታ ሂሳቦች ስላሉበት፣ ገዳይ ፣ አስገዳይና ተባባሪዎች መጀመሪያ በህግ ፊት ሂሳቡን ማወራረድ ግድ ይላል፡፡ የትናንቱ ሹም ፣ የዛሬው ታጋጅና ተሳዳጅ ፣ የነገው የህሊናና የእስር ቤት ታራሚ ለመሆን መፍጠን እርግማን ነው፡፡

ግለሰቦችን በመሾምና በመሻር የወላይታን የክልል ጥያቄ ማዳፈን ግን ፈጽሞ አይቻልም!!!

ወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት