ከጨፈንበት ዐይናችንን ስንገልጥ ብዙ ሺ የልዩ ኃይል ክ/ጦር ጠበቀን!?
ነሐሴ 18 2012ዓ.ም
የዎላይታ ብሔር በክልል ደረጃ ለመዋቀር በሕግ አግባብ ላቀረበው ጥያቄ ሠላማዊና ሕጋዊ መንገዶችን ብቻ ምርጫው አድርጎል፡፡ የዶ/ር አብይ መንግሥት (ለውጥ) ሲመጣ ብሔሩ የነበረው ሚና ከማንም የሚያንስ አይደለም፡፡
ደስ በሚል መልኩ የተጀመረውና ምህዳሩን ያሰፋው የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጭላንጭል ወደ ዎላይታ ሲደርስ ተቀልብሷል፡፡ ኢቲቪ፣ ፋና፣ ዋልታ ወዘተ ሙያዊ ግዴታቸውን አልወጡም፤ የክልል ጥያቄ ጉዳይ ሲነሳ ይባስ ፊታቸውን አዞሩብን፡፡
አማራጭ ሚዲያ ስንጠቀም ሕወሓት ኦነግ አሸባሪ ወዘተ የሚል ታርጋ ተለጠፈብን፡፡ የአሸባሪነት ዉሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መታወጁ ቀርቶ ነው ወይስ የመረጃ እጥረት ገጥሞኝ ይሁን? 1200 ኪ/ሜ ርቀት ወስደው ፍርጃ አደረጉ፤ የደቡብ ክልል መንግስት ሽብር ከአማቾቻችንና ከዘመዶቻችን ጋር አስተሳሰረ፡፡
ክቡር ጠ/ሚሩ ዎላይታ በመጡበት ጊዜ “አስቡበት፣ ተመካከሩ፣ ፀልዩበት ክልሉ በእጃችሁ ነው” ብለውን አምነን ሁሉንም አድርገናል ግን ከጨፈንበት ዐይናችንን ስንገልጥ ዎላይታ ላይ የአጋዚ መአት የልዩ ኃይል ክ/ጦር ጠበቀን፤ በእጃችሁ ያለ መብታቹ ነው; ወደ ሰማኒያዎቹ ኮሚቴ ሄደ፡፡ ባልጨፈንን፤ ከሲዳማ ጋር አንድ ላይ እናውጅ ነበር፡፡
አሁን በዞናችን የተፈጠረው ያለ መረጋጋት የብሔሩን ሕጋዊ የክልል ጥያቄ በመምራታቸው የታሰሩ አካላት ጉዳይ ነው፡፡ ይህን ክስ በማቋረጥ ከሕዝቡና ከአመራሩ ጋር በግልፅ ተወያይቶ የሟቾችንና የተበዳይ ቤተሰቦችን በመካስ እርቀ ሠላም አውርዶ ብሔሩን በግልፅ ይቅርታ ጠይቆ የብሔሩን የክልል ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡
የዞኑ አሰተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ እንደ ግለሰብም እንደ ቡድንም ሰዎች ናቸውና ከእነ ድክመታቸውም ለዎላይታ ሕዝብ የራሳቸውን የሥራ ዕቅድና ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ በነፍሳቸው ተወራርደው የብሔሩን የክልል ጥያቄ መርተዋል፡፡ ለዚህ ጥሬ ሀቅ ሌላ ማስረጃ ሳያስፈልግ ሲነኩ ለመትረየስ ደረቱን የሰጠው የዎላይታ ሕዝብ ምስክር ነው፡፡
በእነዚህ ልጆች ላይ የተጀመረው ክስ ቀጥሎ ዕድሜ ልክ የእስራት ቅጣት ወይም ሞት ተፈርዶባቸው ቢቀር ነገ ማን መጥቶ ለሕዝቡ ሊሰራ ነው? እነ እንትና ለሕዝብ ሰርተው መጨረሻቸው ምን ሆኗል? የሚለውን ያስብና ማንም ይፈራል፣ ይሸማቀቃል፣ አይሰራም፡፡
ፍርድ ቤት የወሰነውን የዋስትና ጥያቄ በይግባኝ ደረጃ ለማየት የግዛት ሥልጣን ያለው በክልል ም/ቤት እውቅና የተቋቋመው የክልል ጠቅላይ ፍ/ቤት ዎላይታ ምድብ ችሎት እያለ ጉዳዩን ወደ አዋሳ መውሰድ ምን የሚሉት ነው? በዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነት እመኑ፡፡ ለሁላችንም ከፈጣሪ በታች ዋስትናችን ፍ/ቤት ነው፡፡ አሁን መፀዳጃ ድረስ የሚያጅበው ወታደር መልሶ የሚያስር መሆኑን መረዳት ይጠቅማል፤ የነገውን የእናንተን ማን ያውቃል፡፡
ጥፋቶች ቢኖሩስ ለማን አሳልፈን ሰጠን? የዎላይታ ጎዳና ቀይ ብጫ ጥቁር ቀለምና የባንዲራ ጨርቅ ለበሰ ተብሎ? ትላንት የሲዳማ ዞን አስተዳደር ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽሞ በዞኑ ሥራ አስፈፃሚዎች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ለምን አልተወሰደባቸውም? የአዲስ አበባ ጎዳናዎች የመንገዱ መሻገሪያ ዜብራ ሳይቀር የኦነግን የባንዲራ ቀለም ተቀብቶ አሸብርቆ አልነበረም?
ቀይ ብጫ ጥቁር የክልል ጥያቄ ሲመለስ ባንዲራችን ይሆናል፤ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 26 መሠረት የዝግጅት ተግባራት አያስቀጡም ነበር ግን ቆይ በደቡብ ብልጽግና የዎላይታ ክልል ምስረታ ዝግጅትም ወንጀል ሆነ? ደቡብ እየፈረሰም ዎላይታን በእኩል ዐይን ማዬት ተስኖታል?
በአፄው ዘመን ዎላይታዎች የንግሥና ሥርዓታቸውን ለመመለስ አቅደዋል ተብሎ የዎላይታ ትላልቅ አባቶች በሀሰት ክስ ዙፋን ችሎት ቆመው ዕድሜ ልክ ፍርድ የተፈረደባቸውን ታሪክ መድገም የለብንም፤ እነ ቀኛዝማች ዋዳ እዛው እሥር ቤት ሞተዋል፡፡ ይህ ድርጊትና ፍረጃ በእኔ ላይ ቢሆንስ ብሎ ማሰብን ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉ በላይ ለትውልድ ግፍም በደልም ሀጢያትም ነው፡፡
ጭቆና ሲበዛ ኢ-ፍትሐዊነት ሲበረታ ለዘመናት አስተዳደራዊ በደል ተሸክመን ኖረናል፡፡ አሁን ግን በቃን፡፡ እያበቃለት ካለው የደቡብ ክልል ስንወጣ ግን በፍጹም ነጥብ መጣል አንፈልግም ፤ አንጥልምም፡፡ ይህ ባይሆን ግን የፈሰሰው የሰማዕታት ደም ላይ መራመድና ለትውልዳችንም እርግማን ነው፡፡ ታሪካዊ ተወቃሽነትም በጋራ አለብን፡፡
ሃኮ አይሶ አዚናይ
የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት እባኳችሁን ሕዝቡን አድምጡልን፣ ስሙት፣ አክብሩትም፤ አስከብሩትም፡፡ መታወቂያ ብቻ መቀየር በቂ አይደለም አስተሳሰባችሁንም ማዘመን ጥሩ ነው፡፡ እልህ የአምባገነንነት ታላቁ ልጅ ነው፡፡ ከልምዳችሁ አንፃር ቻይና ሆዴ ሰፊ ሁኑ፡፡ ለሀገራችሁና ለራሳችሁ ይጠቅማል፡፡
እኛ ሰው በነፍስ የተቃጠለብን፣ በመሬት ሬሳ የተጎተተብን፣ አስተምረን የተሰደብን፣ አልብሰን የተናቅን፣ አጥምቀን የተካድን፣ የሰው ቤት ገንብተን የማንጠግብ ባዶ ሜዳ የቀረን፣ ከቀንድነት ወደ ጭራነት ያመጡን፣ አያቶቻችን በአውሮፕላን በሬው አባቶቻችንን ወደ መኪና ያወረዱብን፣ ዱቄትን በቆጮ ልዋጭ ሲገበያዩ በራሳቸው ገንዘብ በማርጯ የነገዱ የእነዚያ የነገሥታቱ ልጆችኮ ነን እኛ!!!
ብቻችን ሀገር ብንሆን ከማንም አናንስም እንኳን በክልል ተደራጅተን!! በቃ ተውን ልቀቁን ከደቡብ የጠለፋ ጋብቻ ፍቱን አንጀታችን አሯል፡፡
የዎላይታን የሃይማኖት አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ለማናገር ያልፈቀዱ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ ድፍረቱን ከየት ያገኙ መሰላችሁ? ድፍን የነበረው ዎላይታ የተባለ ዕንቁላል ተበስቶ እኛ መከፋፈላችንን አይተውት እንጂ፡፡ እነሱ በድምር ከወከሉት ሕዝብ በላይ ከኃላ የያዘ፣ ደቡብንም ቢሆን ጠፍጥፎ የሰራትና የመራት ሕዝብ ተወካዮች መሆናቸውን በተረዱና ተከብረው ባስከበሩን፡፡ ” ዎኒካ አዬሲ ባይና ሳጋዮይ ናኤሲ ቄሲያ ሜንቴሲ ጊዳ” ያሳፍራል፡፡
ስለዚህ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት እባኳችሁን በድጋሚ ሕዝቡን አድምጡልን፡፡ ስሙት፤ አክብሩትም፤ አስከብሩትም፡፡ ባለመስማማት በወረዳ አትከፋፍሉን፡፡ የዎላይታን ብሔር ከከፍታ ጉዞ አታስቀሩት፡፡ ይልቅ የድርሻችሁን ተወጡ፡፡
ጥያቄያችን የዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ዋና ከተማ ዎላይታ ሶዶ፣ ቀይ ቢጫ ጥቁር ባንዲራችን ነው፡፡ በዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ስምና ባንዲራ ሥር በዞን ደረጃ እደራጃለሁ ባይ ካለ u welcome ብለናል፡፡
ሀገር ለነበረች ዎላይታ ክልል መሆን ሲያንስ ነው፡፡
በደም የተፃፈው የወላይታ የክልል ጥያቄ አፈፃፀሙ ይፍጠን!!!
ኮርሚቻ ሞቶሌ – ጦና