4ኪሎ በዎላይታ ህዝብ የክልል ጥያቄ ጉዳይ ላይ ህገመንግስቱን ያክብር ያስከብር!!
ነሐሴ 15 2012ዓ.ም
አሁን ላይ የዎላይታ ህዝብ በ4ኪሎ ግራ የተጋባ ቦቶሊካ ውስጥ ገብቶ የመፈትፈት የፍላጎት ግጭትም (conflict of interest) ሆነ ጊዜ የለውም:: ይልቅ የዎላይታ ህዝብ ብቸኛ ፍላጎት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በዘለቀ መዋቅራዊና ስርዓታዊ ጭቆናና ጫና የደቀቀ ኢኮኖሚውን እንደገና እንዲያንሰራራ በማድረግ ማህበራዊ እውነታውን በዘላቂነት መቀየር ብቻ ነው::
ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስፈልገው ከዚህ ዘመናትን የተሻገረ ጭቆና የሚላቀቅበት: የራሱን የልማት አጀንዳዎችና ፕሮጀክቶች ያለ ሌላ አካል ይሁኝታ ወይም ክልከላ (without someone else’s goodwill) በራሱ አቅዶና ያለውን የተፈጥሮና የሰው ሀይል ሀብቶች ተጠቅሞ ተግብሮ የራሱን አከባቢ ከድህነት በማላቀቅ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችም ጋር በጋራ በመሆን ሀገራችንን ኢትዮጵያን ወደተሻለ የእድገት ጎዳና ለማስመረሽ የራሱን የጎላ አበርክቶት ለማድረግ የሚያስችለውንና ብቸኛው መንገድ የሆነውን ህገመንግስቱም ያጎናፀፈውን የራሱ የሆነ የክልል አደረጃጀት መዋቅር ነው:: ኢትዮጵያ ልታድግም ሆነ ልትበለፅግ የምትችለው ዎላይታ ሲያድግና ሲበለፅግ ብቻ ነው::
ከዚህ መስመር ውጭ ለዎላይታ ህዝብ በየትኛውም አካል ሊቀርብ የሚችል የተሻለ አማራጭ አይኖርም:: ከዚህ በፊት ላለፉት ሁለትና ሦስት አስርታት ሲደረግ እንደነበረው የዎላይታ ህዝብ እየደኸየ በዎላይታ ህዝብ ስም የተወከሉ የአከባቢው ባለስልጣናትም ሆነ የሌሎች አከባቢዎች ባለስልጣናት በዎላይታ ህዝብ የልማት በጀት የሚበለፅጉበት እውነታ ከዚህ በኋላ ቦታም እድሉም የማይኖረው ያለፈ ታሪክ ነው::
ስለዚህ 4ኪሎ ረጃጆም እጆቹን ተጠቅሞ የዎላይታን ህዝብ ህገመንግስታዊ መብትና ስልጣን ለመንጠቅና የህዝቡን ድምፅ በሀይል ለማፈን የሚያደርገው መውተርተር ሀገር የማያሻግርና የማያረጋጋ: በህዝቦችም መካከል ሰላምና መተማመንን የማይፈጥር የሀገር ሀላፊነት ካለበት አካል የማይጠበቅ ተግባር በመሆኑ እጁን ይሰብስብ: ህገመንግስቱንም በማክበር የዎላይታን ህዝብ የሚመለከቱ ህገመንግስታዊ ውሳኔዎችን ለራሱ ለዎላይታ ህዝብ ብቻ በመተው እንደ ፌዴሬሽኑ የበላይ አካል ህገመንግስቱን ያስከብር::