ጭንጋፍ አክልሉ ለማ – የአዕምሮ የዕውቀትና የምግባር ድኩማን ምሳሌ
መስከረም 30 2015ዓም
በክብረአብ ደምሴ
ለሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ተፈጥሮ ከለገሰችው ፀጋዎች ትልቁና ዋነኛው ጎጂና ጠቃሚውን ለይቶ ለማወቅ በሚያስችለው አዕምሮ መታደሉ ነው፡፡ አዕምሮ ደግሞ ለዕድገቱ ጤናማ ምግብ ያስፈልገዋል፤ የአዕምሮ ምግብ በማስረጃ የተደገፈ መረጃ ነው፤ ለዛ ነው ፈጣሪ ክፉንና ደጉን ለመለየት የሚያስችል አዕምሮ የሰጠው፤ የሆነው ሆኖ ከዚህ ቀደም የመቀንጨር ችግር በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ይስተዋል ነበር፤ የአክልሉ ለማ ግላዊ የአዕምሮ መቀንጨር ከዚህ የባሰ ነው፤ ለደቡብ ኢትዮጵያ ሆነ ለወላይታ ዳፋ ፈጥሮአል፤ የጭንጋፍ አክልሉ ለማ እና የወላይታ የብልፅግና ካድሬ መገልማት ለወላይታ አንደ አትሌቲክሱ አሎሎ ሸክም ሆነዋል፡፡
አክልሉ ለማ የአብይን “እናቴ የሰባት ዓመት ልጅ እያለሁ ነገረችኝን” የሥልጣን ልክፍት ለማስጠበቅ በማይገባው ጦርነት በሚማገደው አምራች የወላይታ ወጣት ማለቅ እንዲሁም ከአንድ ሺ በላይ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና ውጪ በማድረግ የወላይታን ወጣት ተስፋ በማስቆረጥ ወደ ጦርነት ለመማገድ የሚደረገውን የብልፅግና እና የእናውቅልሃለን ባዮች ፖለቲካዊ ሸፍጥ ተሸካሚ በመሆን አሀዱ ብሎ 34ሚሊዮን ለጥቆም ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ለወላይታ የተበጀተውን መንግስታዊ በጀት “አማራ” ነን የሚሉት እንኳ አይመለከተንም ለሚሉት ጦርነት የሚቸር የአዕምሮና የዕውቀት ድኩማን እና የአቶ የሀይለማሪያም ደሳለኝ አንድ ለአምስት ጥፍነጋ የደኢህዴን ጭንጋፍ ነው፡፡
በወላይታ የሀላፊነት ቦታዎች ከተኮለኮሉ “አዋቂ” ነን ባዮች በተጨማሪ ለማህበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ ከመትጋት ይልቅ የሥልጣን ወረፋ ግፍያ ጠባቂ ሆድ አደር ልሂቃን ጉዳይም አሳሳቢ ነው፤ ከሰብአዊነትና ከሰብአዊነት ምግባር የነጠፉ ፣ ከምክንያታዊነትና ሳይንሳዊ አመክንዮ የፀዱ፣ በጥላቻ የነተቡ ሳይቸግራቸው በፈቃደኝነት ከግፈኞች ጋር የቆሙ ልህቃን መብዛት ማህበረሰባዊ መገልማት ውስጥ መግባት አመላካች እንዳይሆን ያሰጋል፤ ይህም ደግሞ ሌላኛው የአዕምሮ መላሸቅ ነው፡፡ እንዴት ተማርኩ የሚለው አመዛዝኖ የማሰቢያ አዕምሮ ያጣል? የተማረውስ ለማነው? ለምንድነው? በተለይም በማህበረሰብ ሳይንስ ትምህርት እዚህኛው እርከን ላይ ደርሻለሁ የሚለው ከአክልሉ ለማ የአዕምሮና የዕውቀት ድኩማንነት እንዴት ተለይቶ ይታያል?
የወላይታ ታዳጊዎች በአዲስ አበባ ጎዳናና በትላልቅ የአገሪቱ ከተሞች “ተመዘን” እያሉ ረሃባቸውን ለማስታገስ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት አክልሉ ለማ ብልፅግና በትግራይ ህዝብ ላይ ላወጀው ጦርነት እነሆ ሲል ሚሊዮኖችን ብር ችሮአል፤ የትግራይን የዘር ማጥፋት በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ፣ የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠውን የመኖር ዕድል መነጠቁ ሳያንስ ከህልፈቱ በኋላ እንኳን ሬሳዊ ክብርን ለመንፈግ የደፈረ አሬመንያዊነትን ለማሽሞንሞን አክልሉ ለማ የሚሄደው የወል እብደት ርቀት የካድሬውን አድርባይነት እና የአዕምሮ መቀንጨር ያሳያል፤ አክልሉ አለማም ግን ቆርቁዟል፡፡