እርግማን በቀለና የጉታራው መዘዝ – ከዓይን እማኝ
ነሐሴ 12 2012ዓ.ም
ክፍል 1
በዎላይታ ሕዝብ ላይ የአቢይ አምባገነናዊ መንግስት የሚያደርሰዉን ሞትና ማቁሰል እንዲሁም ሕገመንግስቱ ያጎናጸፈዉን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተለያዩ መልክ ማፈንን ቀጥሎታል። በርካታ በመንግስት የታገዙ ግድያዎች በኢትዮጵያ ሀገር በተለይ የNobel ተሸላሚዉ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በመንግስት ቀጥተኛ ተዋናይነት ተፈጽመዋል። ይህንን ድርጊት ማን እንደፈጸመ ሕዝቡ ጠንቅቆ ብያዉቅም መንግስት ያለከልካይ በሚቖጣጠራቸው ሚዲያዎች ሕዝብን ደጋግሞ እየዋሸ ይገኛል። አንዳንድ ወንጀሎችን በሟቾች ላይ ያላክካል፤ ሟች ራሱን አይከለክልም፤ አላደረኩም አልፈጸሙኩም አይልም።
እነ አምባቸዉን አሳምነዉ ገደለ ተባለ፤ አሳምነው ተገደለ። ግን እዉነታዉን የመናገር አንደበቱ ለአንደና ለመጨረሻ ተቆለፈ። ለትወና የተመረጠ የአቢይ አገልጋዮች ሟቾች እስትንፋሳቸዉ ገና እንደተለያቸዉ ድስኩሩን ነበር የጀመሩት። በዚህ ዘመቻ መፈንቀለ ክልላዊ መንግስት በማካሄድ የቱቦ አመራሮችን በአማራ ክልል ዘረጋቸዉ።
ኢ/ር ስመኘዉም ራሱን በራሱ አጠፋ ሲል የዋህ መስለን ዝም አልን።
በየክረምቱ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን በልቶ የለመደዉ ቡዳ በወርሃ ነሐሴ 2012 ዓ.ም ወደዎላይታ ነበር የወረደዉ። ቅንብሩን ከዉዳቂ ደቡብ ክልል የቱቦ አመራር ርዕስቱ ይርዳዉ፣ ከፀጥታ አጨናጋፊዉ አለማየሁ እና ዥንጉርጉር ፣ አስመሳይና ከከሀዲ ተስፋዬ ይገዙና በአቢይ አጋፋሪ ተክለወልድ አጥናፉና ሌሎች (እናንተ ማካተት ትችላላችሁ) ባንዳዎች ጋር በመሆን ዎላይታ የጠየቀዉን የሕዝብ ጥያቄ ያንፀባረቁ የሕዝብ ልጆችን ለመብላት በዎላይታ ሶዶ ጉታራ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የተሰበሰቡት ምርጦችን ለመብላት ጦር ላከ። እነኝህ ስብስቦች በእዉነት ምርጥ ትዉልድ ናቸዉ ሲባል የሕግ ምሁራን ፣የዩንቨርስቲ መምህራን ፣ምርጥና ተጽእኖ ፈጣሪ activists ፣ዎሕዴግና ዎብን የወከሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አርቆ አሳቢ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በትምህርት ደረጃም ልህቃንና ከተለያዩ ሙያ የተመረቁ ተቆርቋሪዎች ነበሩ።
የዓይን እማኙ በሥፍራዉ የነበረዉን ወታደራዊ ከበባ እንዲህ ሲል ያስረዳል። “ስብሰባዉን ከሚሳተፉት ከአንድ ግለሰብ ጋር ነበርኩኝ፤ ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ ከሌሎች ተሰብሳቢዎችን ቀድመን ነበር የደረስነዉ። አዳራሹ አከባቢ ሁለት ተሰብሳቢዎችን በግምት 50 ሜትር ርቀት ያህል አየንና ሌሎቹ እስክደርሱ ጉታራ ግቢ የሚሸጠዉን የጀበና ቡና ለመጠጣት ተቀምጠናል። ግን እኛ ለቡና ስንወጣ አንድ ተሰብሳቢም አከባቢዉን በመቀኘት አኳኋን በደአደራሹ ሲገባ ተመልክችያለሁ፤ ግን መጨረሻ ላይ እገታዉ ሲጠናቀቅ ከተያዙት መሀል አልነበረም። በረከት በቀለ የተባለዉም ተሳታፊ ቢሆንም በሥፍራዉ ፈጽሞ አልተገኘም። ይህ በብዙሃን ዘንድ ጥያቄ ፈጥሮታል፤ ምላሽም ማግኘት ያለበት ጉዳይ ነዉ።
ቡና እየጠጣን እያለን አቶ ዳጋቶ ኩምቤ፣ ሐብታሙ ጢሞቴዎስ እና ለሎች ለስብሰባ ሲደርሱ ጓደኛየም ተነስቶ ገባ። ማህበራዊ ሚዲያ እየተመለከትኩ ብቻዬን በቦታዉ ሆኜ አከባቢውን እቃኝ ነበር። ተሰብሳቢዎች እንደገቡ በግምት ከ10 ደቂቃ በኋላ ጉታራ አጥር ዙሪያና ሕንፃዉ በወታደራዊ ሀይል ተከበበ፤ እኛም ተከበብን፤ ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ እንዳናደርግ ፎቶም እንዳናነሳ አስጠነቀቁን።
በስብሰባው አዳራሽ ዉስጥ እነማን ነበሩ? ብዬ በኋላ ለመጠየቅ በቻልኩት መሠረት አቶ ዳጋቶ ኩምቤ፣ አቶ ጥበቡ ዮሐንስ፣ አቶ ሐብታሙ ጢሞቴዎስ፣ አቶ ሚካኤል ሣኦል፣ ወ/ሮ ፀሐይ ገ/ሚካኤል፣ አቶ ጎበዜ ጎዳና፣ አቶ አሸናፊ ከበደ ፣ዶ/ር ቢሥራት ኤሊያስ፣ ጎበዘ አበራ፣ እቴነሽ ኤሊያስ፣አቶ ባታላ ባራና፣አቶ አክልሉ…..፣ አቶ ቅዱስ መስቀሌ፣ አቶ ተከተል ላበና፣ አቶ መብራቱ…አቶ ምህረቱ ኩኬ፣አቶ ሙሉነህ ወ/ፃድቅ፣ አቶ ተስፋዬ አበበ እና ለሎቹ ሲሆኑ እገታ ዉስጥ ግን የመኪና አሽከርካሪ ታከለ እና የፊልም ባለሞያው ይገኝበታል፤ በጥቅሉ ሞቶሎሚ አዳራሽ የተገኙ ሃያ ነበሩ።
ወደ አዳራሽ ዉስጥ የገቡት ጦር ሠራዊቱ በግምት ወደሃምሳ ይደርሳሉ፤ እንደገቡ መሣሪያ ግንባራችን ላይ ወደሩ፣ ሞባይል መሬት ላይ እጅ በጠረጴዛና በደረት እንዲሆን ወታደራዊ ትዕዛዝ አስተላለፉ። “ማንኛውም እንቅስቃሴ ካለ እንጠፋፋለን” ፣ “መሣሪያ የያዜ ሰዉ ካለ ቶሎ እንዲናገር” አሉ፤ አዳራሹ በዝምታ ተዋጠ። Operation መሪዉም ወደ አዳራሹ ገባና “ተረጋጉ በቁጥጥር ሥር ዉላችኋል” በማለት አሸበረ።
አቶ ዳጋቶም እጁን ሳይፈራ አነሳና “ስለምታደርጉት ከበባ በትክክል አዉቃችኋል? ይህ በዞን አስተዳዳሪና በሌሎች መንግስት አመራሮች የሚመራ ስብሰባ ነዉ” ሲል operation መሪዉም የተከበሩ የዞን አስተዳዳሪ እኛ የታዘዝነዉን ነዉ የምናደርገዉ በማለት አረጋገጠላቸዉ። ምናልባት ተሳስተን እንደሆነ ብለዉ ደቡብ ክልል አከባቢ ፊት ለፊታቸዉ ሆኖ ደዉሎ ነበር “የታዘዝከዉን ፈጽም” ሲል ወታደራዊ ትዕዛዝ ጠበቅ አደረገ። ለሁለት ተያይዘዉ ወደዉጪ እንድወጡ ተነገረን። ከሕዝብ እይታ ደብቆ ለመዉሰድ በራሳቸዉ ሽፍን መኪና ለማስገባት ሲሞክሩ አክትብስትና የዎሕዴግ ወጣት ክንፍ ሰብሳቢ ዬላጋ አሸናፊ ከበደ “በእግሬ እሄዳለሁ በመኪናችሁ አልሳፈርም” ብሎ ታገለ። በመጨረሻ በሀይል በመኪናቸዉ ዉስጥ አስገቡትና ለአሽከርካሪዎች ትዕዛዝ በእኩል ፍጥነት እንድጓዙ ተሰጠ። በነገራችን አብዘኞቹን መኪና ለዚህ ተልዕኮ ያመቻቸዉ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨረሲቲ ነው፡፡
መትሪየስ የጫኑ መኪናዎች ታጅበዉ ከጉታራ ግቢ ሲያስወጡአቸዉ በብዙዎች እይታ ገቡ።እኔም የዎብን ፓርቲ ተወካይ አቶ ጎበዘን በክፍት መኪና የተጫነዉን ለማየት ቻልኩኝ። እንደ ኢሕአፓ በአንድነት ልረሽኗአቸዉ እንደሆነ ተሰማኝ እና መረጃ ተለዋወጥን። ወዲያዉኑ መሪዎቻቸዉ ስለመታገታቸዉና መድረሻቸዉን ያላወቁ የዎላይታ ሕዝብ በአንድነት ተነስተዉ መንገድ በመዝጋት ተቃዉሞአቸዉን ገለጹ። አልሞ ተኳሾቹ በተኩስ ሠላማዊ ሠልፈኞችም ሆነ ስለሠልፉ ምንም መረጃ የሌላቸዉን ሱቅ ዳቦ ለመግዛት የወጡ ሕጻናትን፣ የወሊድ ክትትል የሚያደርጉ ነፍሰ ጡር እናቶች ሆዳቸዉ ላይ ተኩሰዉ፣ጎ ዳና ላይ የሚዞሩ የአእምሮ ሕሙማንን ጭምር ጭንቅላታቸዉን በማፍረስ እንደወጡ አስቀሩ። አስከሬናቸዉም እንዳይነሳ ሕዝብ ተከለከለ። ተቃዉሞም ግድያዉም ለአምስት ቀን ዘለቀ። የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጣ። ሆስፒታሎች በጥይት በተመቱ ተጨናነቁ። ከ34 በላይ የሚደርሱ ንጹሃን የዎላይታ ሠላማዊ ታገዮች በደም መጣጩ በብልፅግናው የአቢይ አህመድና በአሽከሮቻቸዉ ዳግም ላይመለሱ እስከወዲያኛው አሸለቡ። ወታደሮቹ ገና እንገላለን እንዳሉም ናቸዉ። በወታደሮቹም መሀል ይህንን ግዲያ ፀረ-ዎላይታ አመለካከት ካላቸዉ ብሔር የመጡ እንዳከናወኑ ግልጽ መረጃዎች አሉ። የዎላይታ ሕዝብ ሥልጡን መንግስት ደግሞ ያልሰለጠነ አረመኔ መሆኑ የደም መስዋዕትነት እያስከፈለ ይገኛል።
የፍርድ ቤት ሂዴት ምን ይመስላል? በክፍል ሁለት እንቃኘዋለን…