ነፃነት በሌለበት ግፍ እንደፍትሐዊነት ይታያል!!!
ነሐሴ 11 2012ዓ.ም
ለዓመታት በአገዛዝ ሥር ተነጥፎ በባሕል ሰንሰለት በይሉኝታና “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም” በሚል ምርጊት ታፍኖ፣ አዕምሮ የማሰብ ተግባሩን አቁሞ፣ በፍርሃትና በትዕዛዝ እየተነዳ፣ ለዕለት ጉርሱ ለዓመት ልብሱ ብቻ ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል በማለት ራሱን እያታለለ ጌቶችን በሚያስደስትበት የአገዛዝ ሥርዓት እኩልነት የለም፤ ነፃነት የለም፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጭቆና ጭቆናን ይወልዳል፤መሪው ሹማምንቱን ይጨቁናል፤ ሹማምንቱ ሕዝብን ይጨቁናሉ፤ ሕዝብም እርስበርሱ ባለው የበላይነት መጠን ይጨቋቆናል፤ የሚጨቁኑት ሌላ ሰው ከጠፋ ልጆችና ሚስቶች አሉ፤ እንዲህ እያለ ጭቆና ባህል ይሆናል፡፡
ሰው ተምሮ እንዳያውቅና እንዳይጠይቅ፣ አዕምሮ በነፃነት እንዳይበለፅግ ሆን ተብሎ ጥያቄ በመጠየቅና በማወቅ ላይ የማጥላላት ዘመቻ ይደረጋል፤ ሰዎች እንዳያውቁ፣ እንዳያስቡና እንዳይጠይቁ እየተደረጉ በልማድና በባሕል ተጭነው ለአገዛዝ እንዲመቹ ይደረጋሉ፤ መሪውና ሹማምንቱ አሮገውን ልማድና ባሕል አዲስ ካባ እያለባበሱ ይቀጥላሉ፤ ስለ ነፀነት የሚናገሩ ሰዎች ብቅ ሲሉ ኩርኩም ከያለበት ይደርስባቸዋል፤ መሪዎችና ሹማምንትም ሕዝቡን በነፃነት ሰባኪዎች ላይ ያስነሱባቸውና ለጥቃት ያመቻቿዋል፤ በዚያን ጊዜ ነው ሕዝቡ ወዳጁንና ባለጋራውን አጥርቶ ማወቅ ያለበት፡፡
የነፃነት ጥያቄ እየተስፋፋ ሲሄድ ሰዎች ሀሳባቸውንና ስሜታቸውን እንደልባቸው መግለፅ ሲጀምሩ የእኩልነት ጥያቄ፣ የፍትህ ጥያቄ፣ የአገር ሀብት ድልድል ጥያቄና ሌሎችም የሕዝብ ጉዳዮች በአደባባይ መነሳት ይጀምራሉ፤ ሕዝብ መንቃት ጀመረ የሚባለው እዚህ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነው፤ ቀስ በቀስ በቁርጠኝነትና በመንፈሳዊ ወኔ እየተደራጁና ኃይል እየጨመሩ ሲበረቱ የነፃነትና የእኩልነት መብቶች ይረጋገጣሉ፤ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ግን ቀላል አይደለም፤ ተብትበው የሚይዙ ባሕላዊ ችግሮች ሞልተዋል፤ በግልም ይሁን በጋራ መብትን ለማስከበር በቆራጥነት ከመቆም ይልቅ መቅለስለስ፣ መለመን፣ መለማመጥ፣ ኃላፊነትንና ግዴታን አለመቀበል ለጊዜው የሚያዋጡ ዘዴዎች መስለው ይታያሉ፡፡
ነፃነት የሌለው ሰው አንደተመረገ ጋን ነው፤ ውስጡ ምን እንዳለ አይታወቅም፤ ነፃነት በሌለበት ጉልበተኛው የሚናገረው ሐሰት እንደ እውነት ይቆጠራል፤ የጉልበተኛው ግፍ እንደፍትሐዊነት ይታያል፤ ጥሩ ሀሳብ፣ ማህበረሰቡን የሚጠቅም ሀሳብ እንደጦር ይፈራል፤ የሚያምኑት ከተገኘ የልብን መነጋገር የሚቻለው በሹክሹክታ ብቻ ይሆናል፤ ግልጽነት አደገኛ እየሆነ ማድበስበስና ማጭበርበር ልማድ እየሆነ ይሄዳል፤ መተማመን ያዳግታል፤ ልበ ሙሉ ሆኖ ሀሳብን መግለፅ ያስፈራል፤ እንዲህ ያለው ሁኔታ የእድገትና የመሻሻል ፀር ነው፡፡
(ምንጭ፡- ሥልጣን ባህልና አገዛዝ ፖሊቲካና ምርጫ – ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም)