በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ በማንሳት የሚንቀሳቀሰው የዞኑ አመራርና ሕዝብ በሕገ መንግስቱ ድንጋጌ መሠረት ተገቢ መልስ በሰላማዊ አግባብ ሊሰጠው ይገባል!
ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የተሰጠመግለጫ
Ethiopian Social Democratic Party
August 12, 2020
የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልላዊ መንግሥት የማቋቋም መብት እንዳላቸው በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 47(2) ላይ ተደንግጓል፡፡ ይህን ህገ – መንግሥታዊ መብት ለማስከበር ከአሥር በላይ የሆኑ የደቡብ ብሔራዊ ክልል ዞኖች ፣ በየዞናቸው ም/ቤት በማስወሰን ለክልሉ ም/ቤት ጥያቄዎቻቸውን ማቅረባቸውንና ውሳኔ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ከተለያዩ ምንጮች ስንሰማ ቆይተናል፡፡
እስከ አሁን ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ዞኖች መካካል በህገ መንግሥቱ መሰረት ሕዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ በክልልነት የመደራጀት መብት የተከበረለት የሲዳማ ዞን ብቻ ሲሆን፣ የሌሎች ዞኖችን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን በቡድን /በክላስተር /በማሰባሰብ ከአንድ በላይ በሚሆኑ ክልሎች ለማደራጀት በመንግሥት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ በመንግስት እየተደረገ ያለውን በክላስተር የማደራጀትን አማራጭ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ ዞኖች እየታዩ ናቸው። በመሆኑም ከሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ አልተሰጠንም ከሚል ተስፋ መቁረጥ ተነስቶ፣ ሕዝቡ ወደ ግጭት እንዳይገባ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ሥጋቱን ገልጾአል ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የተፈራው ስጋት እውን ሁኖ የወላይታ ዞን አመራር የመንግስትን የመፍትሄ አቅጣጫ በመቃወም የምክክር ስብሰባ እያደረገ ባለበት ወቅት መንግስት በወሰደው እርምጃ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ተሰምቷል። በዚህ መነሻነትም ሕዝቡ ተቃውሞ እያሰማ እንደሆነና ከፀጥታ አስከባሪ ሀይሎች ጋር በሚፈጠሩ ግጭቾች የሰው ሕይወት እስከ መጥፋት እየደረሰ መሆኑም በእጅጉ አሳስቦናል።
ስለሆነም፣ መንግሥት የጉዳዩን ሰፊ እንደምታ በጥልቀት በመመልከት፣ በዞኑ ለተነሳው ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠት፣ ጥያቄውን በማንገብ ምላሽ ለመሻት የተንቀሳቀሱትን የወላይታ ዞን አመራር አካላትን እና በጉዳዩ ሳቢያ የታሰሩትን ሁሉ በመፍታት፣ ለተከሰተው ችግር ሰላማዊ መፍትሄ በአስቸኳይ እንዲፈልግ ኢሶዴፓ ያሳስባል፡፡ አስተዋዩ ሰፊ የወላይታ ሕዝባችንም ጉዳዩን በወትሮ ጥበቡ በትዕግስት በመያዝ፣ የሰላሚዊ መፍትሄ አካል እንዲሆን ኢሶዴፓ በአክብሮት ጥሪ ያደርጋል!!
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)
ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ