መንግስታዊ ሽብርተኝነት ሀገር ቢያፈርስ እንጂ ሀገር አይገነባም!!!

በራፍኤል አዲሱ

August 10, 2020

በአንድ ከፍተኛ የክልል ባለስልጣን የአፍ ወለምታ ባመለጠ ሚስጢር የተፈጠረ የፖለቲካ ትኩሳት ለማብረድና አጀንዳ ለማስቀየር ተብሎ በውሸት ትርክት ሀገርና ህዝብ እንዲጠብቅ ስልጣንና ሀላፊነት የተሰጠውን የመከላከያ ሰራዊት ወታደር ሉዓላዊ ህዝብ ላይ ተኩሶ እንዲገድል: አካል እንዲያጎድል በማድረግ ለርካሽ የፖለቲካ ቁማር መጠቀሚያ በማድረግ ለመበልፀግ ማሰብ ከጅምሩ የከሸፈ ፖለቲካ መገለጫ ነው::

የንፁሀን ዜጎችን ደም እየጠጡ መበልፀግ ሰይጣንም አልተሳካለትም!! ለሰላማዊና ህገመንግስታዊ የህዝብ ጥያቄ ፖለቲካዊና ህጋዊ መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄውን የደህንነት መልክ እንዲይዝ (securitize) በማድረግ በህገ-ወጥ ቡድን ህዝብ ላይ ፀብ-ጫሪ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ህዝቡን ወደ ስርዓት አልበኝነት ጥግ መገፋፋት anarchist የሆነ ስርዓት መገለጫ ነው:: በዚህ ሂደትም በሚፈጠር የህዝብ ተቃውሞ ከመጠን/ልክ ያለፈ (unproportional force) በመጠቀም አከባቢውን ወደ ቀውስ ቀጠናነት በመቀየር በፍፁም ወታደራዊ አገዛዝ አፍኖ የመግዛት ፍላጎት መቼም ሊሳካ የማይችል የድኩማን ምኞት ነው::

በህገመንግስታዊው አግባብ ካየን ሲዳማ ህጋዊ አስረኛ ክልል በሆነ ግዜ ነው ደቡብ ክልል የሚባል የክልል መዋቅር disolve የተደረገው:: ምክንያቱም የኢፌዴሪ ህገመንግስት ‘የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል’ ብሎ ህጋዊ እውቅና የሰጠው ክልል የቀድሞውን የሲዳማ ዞን ጭምር ያካተተ ነው:: ስለዚህ ሲዳማ የሌለበት አሁን ‘የደቡብ ክልል’ አስተዳደር ነኝ ብሎ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ህገመንግስታዊ እውቅና የሌለው ህገ-ወጥ ቡድን (non-legitimate group) ነው:: በዚህ አሁናዊ እውነታ በቀድሞው የደቡብ ክልል ውስጥ በነበሩ አከባቢዎች የመንግስታዊ አስተዳደር መዋቅር ከፌዴራሉ መንግስት መዋቅር ቀጥሎ ብቸኛ ህጋዊ እውቅ ያለው መንግስታዊ መዋቅር የዞን አስተዳደር መዋቅር ብቻ ነው:: ከዚህ አንፃር ትናንት ጀምሮ በወላይታ ምድርና አከባቢው የተሰማሩ የመከላከያና ህጋዊ ተጠሪነታቸው የማይታወቁ የልዩ ሀይል አባላትን ተጠቅሞ ሰላማዊ ህዝብ በlive ammunition እያስገደለና የአካል ጉድለት እያደረሰ ያለው ቡድን ህገወጥ ቡድን ነው ማለት ነው::

ራሱን የደቡብ ክልል አስተዳደር ብሎ የሚጠራው ይኸው ህገ-ወጥ ቡድን በወላይታ ህዝብ የተመረጡና የህዝቡ ህጋዊ እንደራሴዎች የሆኑ የዎላይታ ዞን ከፍተኛ አመራሮችን የወላይታ ህዝብ የዛሬ አመት (2011) ታህሳስ ወር በዞኑ ምክር ቤት ሙሉ ድምፅ ወስኖ ካነሳው ህገመንግስታዊ የክልል አደረጃጀት ጥያቃ መልስ ማጣት ጋር ተያይዞ በጉዳዩ ለመምከር የተሰበሰቡ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችን በትናንትናው እለት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ በዋና ከተማዋ ሶዶና አከባቢው ባሉ የተለያዩ ከተሞች የተከሰተው አለመረጋጋትና ይህን ተከትሎ ሌሊቱን ከ40 በላይ በሚሆኑ የመከላከያ በተለምዶ ኦራል ተብለው በሚጠሩ የጭነት መኪኖች ከአርባምንጭ ተጓጉዘው በገቡ ህገወጥ ኮማንድ ፖስት የፀጥታ ሀይሎች የተወሰደ ሰላማዊ ሰዎችን በጥይት ተኩሶ የመግደልና አካል የማጉደል እርምጃ በከፍተኛ ደረጃ የሚወገዝ የአምባገነን መንግስት መገለጫ የሆነ ጭካኔ የተሞላው የህዝብንም ህልውና አደጋ የጋረጠበት ተግባርና መንግስታዊ ሽብርተኝነት (State_terrorism) ነው::

የፌዴራሉ መንግስት ለዚህ እየተካሄደ ላለ ህገወጥ የህዝብ ጭፍጨፋ (Wolaita_genocide) ሀላፊነት መውሰድ አለበት:: ሀገር በሁሉም አቅጣጫ በተወጠረችበት በዚህ ግዜ ህገመንግስቱን በጣሰ አካሄድ በsecurity pretext የአንድን ሉዓላዊ ህዝብ ህገመንግስታዊ መብት በሀይል በመጨፍለቅ ወታደራዊ የጭቆና ስርዓትን ለማስፈንና ሀገሪቱ የምትተዳደርበት ህገመንግስት ያጎናፀፈውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመንጠቅ በሀይል የመግዛት አካሄድ መጨረሻው አጠቃላይ ሀገራዊ ውድቀትን ማፋጠን ብቻ ነው የሚሆነው::

Wolaita Today
Pregnant Women Killed
Wolaita Today