ለኢትዮጵያ የህዝቦቿን እኩልነት በተግባር ያረጋገጠ ስርዓት መገንባት ማንነት ተኮር ጥቃቶችን ለማስቀረት ቁልፍ እርምጃ ነው!!
ታህሳስ 16 2013ዓ.ም
በንፁሀን ዜጎች ህይወት የመነገድ ፖለቲካ በቀደሙት 27 አመታት ውስጥ የተረገዘች ቢትሆንም ባለፉት ሁለት አመት ከግማሽ ውስጥ የተወለደች አዲስ ፖለቲካ መጫወቻ ካርድ እንደሆነች ይታወቃል:: አሁን በፍቅር ተንከባክበው እያሳደጓት ያሉ የብልፅግና ፖለቲከኞች ነገ አድጋ ከቁጥጥራቸው ውጭ ስትሆን መዘዟ ምን ሊሆን እንደሚችል እንኳ ለማሰብ ያለመፈለጋቸው ነገር ነገሩን አስፈሪም አሳፋሪም ያደርገዋል::
በአለማችን ታሪክ ክፉ የታሪክ ጠባሳ የተዉ ስርዓቶችን ሳያስተናግዱ ዛሬ ላይ የሰለጠነና ዴሞክራሲያዊ የመንግስት አስተዳደር ስርዓትና የሀገር መልህቅ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት የገነቡ ሀገራት የሉም:: ነገር ግን ያን የታሪክ ጉድፍ እንደኛ ህዝብን ከህዝብ እያቀሳሰሩ ለከሰረና ለከሸፈ ፖለቲካ ማሰንበቻነት ሲጠቀሙበት አይታዩም:: ይልቅ ያለፉት የታሪክ ስህተቶች የፈጠሩትን መቃቃርና ኢፍትሀዊ ስርአታዊ መዋቅሮች በጣጥሰው ጥለው ሁሉም ዜጋ የኔ ብሎ የሚኮራበትን: የቡድንና የግለሰብ መብቶች ሙሉ በሙሉ ሳይሸራረፉ የተከበሩበትን: እና በጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት ምሰሶነት የቆመ የዘመኑን ማህበረሰባዊ ስልጣኔ ደረጃ የሚመጥን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ገነቡ እንጂ::
በሀገራችን ይህን ለማድረግ መፍትሄው በአንድ በኩል የሀገራችንን የተለያዩ ህዝቦች እኩልነት (ፍትሀዊ ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና እንዲሁም የሁሉም ባህልና ቋንቋ በነፃነትና አንዱ ሌላውን ሳይጫን አሊያም ሳይጨፈልቅ በእኩል የሚያድጉበት): የህዝቦችን የማይገረሰስ ተፈጥሯዊ መብት (inalienable rights) እና ስልጣን ማክበርና ይህንኑ በስርዓት ደረጃ የሚያረጋግጥ ፖለቲካዊና ህገመንግስታዊ ስርአት መገንባትና ማጠናከር ያስፈልጋል:: በሌላ በኩል ደግሞ ስርአታዊ የታሪክ በደሎችን እያነሱ ህዝብን ከህዝብ ማጋጨት እንዲሁም አንዱን የጨቋኝ ወገን አድርጎ በመሳል በጥርጣሬ የመተያየት አባዜ መቅረት አለበት::
ሀገራችን ከተገነባችበት ስርአታዊ ኢፍትሃዊነት አንፃር የተለያዩ የሀገራችን ህዝቦች በግዜው በነበሩ ስርዓቶች ታሪካዊ በደል እንደተፈፀመባቸው እየታወቀ አሁን ላይ ሉዓላዊ የሀገራችን ህዝቦች የተጎናፀፉትን ራስን በራስ የማስተዳደር: የራስ ባህልና ቋንቋ እንዲሁም ማንነት በማሳደግ በጋራ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ: ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች የጋራ ተሳትፎና አበርክቶት የሚያደርጉበት ስርአታዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ይበልጥ ሊጎለብት የሚገባው ለቀጣይ ሀገራዊ አብሮነትም ምሰሶ የሆነ ጉዳይ መሆኑን መቀበል መመለሻ የሌለው ብቸኛ አማራጭም ነው::
ይልቅ በሆነ ቡድን ይህንን የሀገሪቱን የተለያዩ ህዝቦች የማይገረሰሱ መብቶች (inalienable rights) ላለመቀበል የሚደረግ መውተርተር ካለ አሁን ላይ በተለያዩ አከባቢዎች ለሚደርሱ ማንነት ተኮር ግጭቶች የግጭት ነጋዴ የሆኑ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እያደረጉት እንዳይሆን ቆም ብሎ ማሰብ ይበጃል:: ከዚህ በተረፈ ለዜጎች ህይወት የሚገባውን ክብር በመስጠት ህግ የማስከበር እርምጃውን ከተቋማዊነት ባለፈ ህብረተሰባዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ እነዚህን አሳፋሪ ማንነት ተኮር ጥቃቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ማስቀረት በየአከባቢው የመንግስት ስልጣን ይዘው የሚገኙ አካላት ሀላፊነት ነው::