በግድ እኛን ሁኑ

Wolaita Today

አንዱአለም ሰ. አበራ

ጥቅምት 14 2013ዓ.ም

አንዳአንድ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የተለያየ ቋንቋ ፣ ባህልና ታሪክ ያላቸዉን ህዝቦች በጉልበት ጨፍልቀዉ አንድ በማድረግ “በግድ እኛን ሁኑ” የሚል ጽንፈኛ አመለካከት አላቸዉ።

“በግድ እኛን ሁኑ” ማለት ሌላ ሳይሆን የራሳችሁን ቋንቋ ፣ ባህልና ማንነት ትታችሁ የእኛን ማንነት በሀይልና በጉልበት ተቀበሉ ማለት ነዉ፤ ይህ አካሄድ ሲበዛ አደገኛ ነዉ። አንድ ቋንቋ ፣አንድ ሀገር ፣ አንድ ሀይማኖት የሚል ተረታ ተረት ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ህያዉ ምስክር ነዉ በተለይም ደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል።

እነዚህ ግለሰቦች ንፁህ ኢትዮጵያዊ ከእኛ በላይ ለአሳር የሚሉ የትህምክተኞችን (አሀዳዊያን) አመለካከት ዶ/ር መረራ ሲገልፃቸው እነዚህ ግለሰቦች “የኢትዮጵያዊነት የምስክር ወረቀት ሰጭና ከልካይ አድርጎ ራሳቸዉን የሾሙ” ይላቸዋል።

ይህ የዘዉግ ጥያቄ ወደ ጥግ መስመር ከመዉሰድ ዉጭ የሚያመጣው አንድም ፖለቲካዊ ፋይዳ የለዉም። ይህንን ሀሳብ የሚያጠነክር የዶ/ር መረራን ትዝብት ላካፍላችሁ “የንጉሱ መንግስት የኤርትራን ፌዴሬሽን በማፍረስ ያገኙት ጀብሃና ሻዕቢያ የተባሉ ተቃዋምዎችን ነዉ። በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ የሌላቸውን ሜጫና ቱለማ የልማት ማህበር መርዎችን በማፈን ያገኘዉ ዉሎ አድሮ የኦሮሞ ነፃ አዉጭ ግንባር (ኦነግ)ን ነዉ። ደርግ በተራዉ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ የሌላቸዉንና በዋናነት በትግራይ ልሂቃን የሚመራዉን ኢህአፓ በማፈን ያገኘዉ ህወሓትን ነዉ። በዘመኑ ይሻላሉ በሚባሉ የኦሮሞ ልሂቃን ጭምር የሚመራዉንና በኦሮሞ አከባቢዎች ሰፍ ሚና የነበራቸዉን መኢሶንን በማፈን ያገኘዉ ለየት ያለ ህልም ያላቸዉን የኦሮሞ ብሔርተኞችን ነዉ።

አሁን ዎላይታን ጨምሮ በተለያዩ ብሔሮች ላይ እየተፈፀመ ያለዉ ይህንኑ ነዉ።

የማንነት ጥያቄ

አንዱአለም ሰ. አበራ

ጥቅምት 17 2013ዓ.ም

“የማንነት” ጥያቄን ያመነጨዉ ህወሓት/ኢህአደግ እንደሆነ የሚሞግቱ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ይህ ትክክል አይደለም፤ በአጭሩ የኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ “የማንነት ጥያቄን ያመነጨዉ ህወሓት/ኢህአደግ ነዉ” ብሎ መሞገት ግን ከምላስ ላይ ፀጉር እንደመንቀል ይቆጠራል።

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ጥንስሱ የተቋጠረዉና የንድፈ ሀሳብ ቀመሩ የተቋጨዉ ገና በ60ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ (#በያ_ትዉልድ) ዉስጥ ሲiሆን ፋና ወጊ በመሆን ቁልፍ ሚና የተጫወቱትም ዋለልኝ መኮንን ፣ ሌንደን ካንኮ (ስለ እሱ በስፋት እመለሳለሁ) ሌሎችም ሲሆኑ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም የነፍስ አባት (ፈጣሪ) ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንብኝም።

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ቀራጮች የተባሉት ደደቢት በረሃ ሳይገቡ እንዲሁም ጠብመንጃ ከመታጠቃቸዉ በፊት የታጠቁትና የተቀረጹት በዋለልኝ መንፈስ ነበር። ህወሓት ላለፉት 27 አመታት በሀገርቱ ያሰፈነዉ የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራል ስርዓትና መንግስታዊ አወቃቀር ፍፁም ተወዳሽና እንከን የለሽ ያደርገዋል ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ነዉ።

ስለዚህ የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም የመንግስት አወቃቀር ወይንም አሃዳዊያን እንደሚሉት “የብሔር ፖለቲካ” ህወሓት/ኢህአደግ እንዳላስጀመረዉ ሁሉ ህወሓት የሚባለው የፖለቲካ ድርጅት ከጠፋ የሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሪዕዮት እንበለው የመንግሰት አወቃቀር አብሮ ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ ከአንበሳ መንጋጋ ስጋን እንደመንጠቅ እቆጥረዋለሁ።

በሀገርቱ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውን የሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ለመደምሰስ ከማሰብ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ከተወጣጡ ተወካዮች ጋር የጋራ መግባባት በመፍጠር እዉነተኛና ትክክለኛ ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ማስቀጠል ሲገባ ህወሓትን በማጥፋት የማንነት ጥያቄ አብሮ ይጠፋል/ያከትማል በሚል አጉል ትርክት በሀገርቱ ጦርነት ማወጅ ትልቅ ስህተት ነዉ።

የብሔር ፖለቲካዉ በያ-ትዉልድ ተፀንሶ ከሞላ ጎደል በህወሓት/ኢህአዴግ ቀጥሎ መጪዉንም ጊዜ ህወሓት/ኢህአዴግ ያጠፋውን ስህተቶች በማረም በብሔር ብሔረሰቦች ፅኑ ትግል ይቀጣጠላል እንጅ በድጋሚ አሀዳዊ መንግስት በኢትዮጵያ ለመመስረት ማለም ቅዠት ነው፤አሀዳዊ መንግስት በኢትዮጵያ ዳግም ላያቆጠቁጥ ከወታደራዊው የደርግ መንግስት ጋር አብሮ ተቀብሮአል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ያላት መፍትሄ ሕብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት ነው፡፡ የወላይታ ብሔር በዚሁ የፌዴራል ሥርዓት ትክክለኛ ዉክልና ሲያገኝ ለኢትዮጵያ ፈውስ ይሆናል፤ “ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ ከbaron prochazka ቀጥሎ በአ** ብሔር/ሕዝብ ላይ ያሴረ ግለሰብ ቢኖር የመኮንን ልጅ  ዋለልኝ  ነው” ብሎ የዕልቂት ከበሮ መደለቅ ዳግም ለመላላጥ ካልሆነ በስተቀር ስንዝር አያስከድም፡፡

ወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት

 

Wolaita Today