የዎላይታ ጀግኖች የሀገርን የግዛት ሉዓላዊነትና የቀጠናውን ሰላም የሚያስከብሩ ተወርዋሪ የጦና ንቦች እንጂ የብልፅግና ፓርቲ የስልጣን ጋሻ ጃግሬዎች አይደሉም!!

ኅዳር 15 2013ዓ.ም

በከሚሴ እና ዎላይታ ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ከመከላከያ ሰራዊቱ በክብር የተሰናበቱ የቀድሞ የሰራዊቱ አባላትን: ተጠባባቂ የመከላከያ ሰራዊቱ አባላትና የአከባቢ ሚሊሻዎችን የብልፅግና ካድሬዎች “60,000 ብር እና ስትመለሱ ቤት መስሪያ ቦታ ይሰጣችኋል” እያሉ እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ለመማገድ እየደለሉ ነው የሚሉ ዜናዎች እየተሰሙ ነው:: በፌዴራሉ የብልፅግና መንግስት “ህግ የማስከበር እርምጃ” በሚል የተጀመረውና የአማራ ክልል ልዩ ሀይልና ሚሊሻን ጨምሮ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በአንድ ጎን: እንዲሁም በሌላ ጎኑ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት: የኦሮሚያና የሱማሊ ክልል ልዩ ሀይሎችን ጥምር በማሳተፍ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሰው አልባ ድሮኖች የአየር ላይ ጥቃት በመታገዝ በህወሓቱ ቡድን የሚመራውን የትግራይ ክልል ልዩ ሀይል የገጠመበት ጦርነት ከተጀመረ ሶስት ሳምንት ቢሞላውም ማብቂያው መች እንደሆነ አይታወቅም::

እነዚህ ሚሊሻዎችና የቀድሞ የሰራዊቱ በክብር ተቀናሽ አባላት እስካመኑበት በዚህ አሰቃቂ ጦርነት በግል ውሳኔያቸው የመሳተፍ መብታቸው የተጠበቀ ነው:: አሜሪካኖቹ እንደዚህ በገንዘብ ተገዝተውና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ተነድተው በጦርነት የሚሳተፉ ወታደሮችን “Mercenaries” (ቅጥረኛ ገዳዮች) ይሏቸዋል:: እነዚህ “ቅጥረኛ ገዳዮች” ምንም አይነት ወገንተኝነት (allegiance) የሌላቸው: ለሀገርና ባንድራ የሚባል ነገር የማያውቁ: ለራሳቸው ክብር የሌላቸውና ገንዘብ እስከተከፈላቸው የትኛውንም ወገን በ’ቅጥረኛ ገዳይ’ነት የሚያገለግሉ እንደሆኑ ይታወቃል:: የእነዚህ ቅጥረኞች ሞትም የሚገደው አካል ስለሌለ በአብዛኛው የፊት ለፊት ተሰላፊ ተደርገው ለወገን ወታደር ፈንጅ ማፅጃነትና የጠላትንም አቅም በመጀመሪያ ለማዳከም ይውላሉ::

የዎላይታን በክብር ከመከላከያ ሰራዊት የተቀነሱ የቀድሞ የሰራዊቱ አባላትን በተመለከተ ግን አንድ ነገር ግልፅ መሆን አለበት:: አሁን ሀገሪቱን እየመራ ያለው የብልፅግና ፓርቲ ባለፉት ሁለት አመት ከግማሽ ግዜ ውስጥ በዎላይታ ተወላጆች ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ላይ እንዲደርስ የፈቀደው ጭፍጨፋ ከዘር ማጥፋት (genocide) የሚስተካከል እንደሆነ ይታወቃል:: ከዚህም በዘለለ ህዝብ በሰላማዊ መንገድ ለጠየቀው ህገመንግስታዊ የክልል ጥያቄ በአደባባይ ነፍሰ ጡር እናትና ህፃናትን በጥይት በመደብደብ ምላሽ እንደሰጠም ይታወቃል:: ከጥይት የተረፉትንም የህዝብ የመብት ጥያቄ ያነሱ አመራሮች: የማህበረሰብ አንቂዎች: ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ለፍርድ አልባ እስር: እንግልት: የተቀነባበሩና በፖለቲካ ፍላጎቶች ለሚነዱ የክስ ሂደቶችና (politically motivated prosecusions): ለስደት በመዳረግ ህዝቡን መሪ አልባ የማድረግ መዋቅራዊ የጭቆና ፖለቲካዊ ሴራው ሰለባ ማድረጉን ቀጥሎበታል::

አሁን ሀገርን የማስተዳደር ስልጣን ድንገት እጁ ላይ የወደቀበት ይህ የብልፅግና አሀዳዊና ፋሽስታዊ ስርዓት እንቅልፍ አጥቶ እየሰራ ካለባቸው ነገሮች አንዱ የዎላይታን ህዝብ ማንነት በሀይል በመጨፍለቅ: ህዝብ እስከዛሬ ከደረሰበት ኢኮኖማያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጭቆና በበለጠ ጥልቅ ድህነት ውስጥ እንዲማቅቅና በሀገሪቱ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ውክልና እንዳይኖረው በማድረግ እንደ ህዝብ ማንነቱን ማጥፋት ነው:: ይህን የሚያደርገውም በዋናነት ህዝብ ያልመረጣቸውን ሆድ-አደርና አድሃሪያን የህዝቡን የአሁንና የቀጣይ ትውልዶችን ድምፅ በመሸጥ ስልጣናቸውን በተላላኪነት የሚያደላድሉ ምስለኔዎችን (አሁን የተሾሙ አይነት ዎዝቶ ዎብሎዎችን) በመጠቀም ነው:: ይህ ነው እንግዲህ የዎላይታ ህዝብ የሀገር ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ለማስከበር ውድ ልጆቹን በገበረ በምላሽ የተሰጠው!! ይኸው የመንግስት አካልም ነው እንግዲህ አሁን በዚህ ትርጉም የለሽ ጦርነት የህዝቡን ጀግና ልጆች ለመማገድ በአንድ ካድሬ የወር የስብሰባ የውሎ አበል ሂሳብ ለመደለል እየተሯሯጠም ያለው::

እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት የሁለት የፖለቲካ ቡድኖች (ብልፅግና እና ህወሓት) የስልጣን የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት አለፍ ሲልም በብቀላና በጥላቻ የታወሩ የተወሰኑ ቡድኖች የ”ርስት የማስመለስ” ዘመቻ እንጂ ሀገር አልተወረረችም የውጭ ጠላትም አልመጣባትም:: ሆኖም የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በትንኮሳ የተነሳ ወደዚህ በእብደት ወደሚነዳ ሀገር አፍራሽና ትርጉም የለሽ የእርስ በርስ ጦርነት መግባቱ በእርግጥ እጅግ አሳዛኝ ነው:: ግን አንድ ግልፅ የሆነ ነገር ቢኖር በዚህ ጦርነት በሁለቱም በኩል ኢትዮጵያዊያን እንደ ዝንብ እየረገፉ ያለበትና ከፍተኛ የሀገርና የህዝብ ሀብት ውድመት እያደረሰ ያለ: ሰብአዊ ጥፋቱም የትዬሌሌ የሆነ አሰቃቂ ጦርነት የመሆኑ እውነታ ነው::

በሌላ ጎኑ ይህ የምልመላ ዘመቻ የሚያሳየው በጦርነቱ ብዙ ሰው እያለቀ መሆኑን እና ጦርነቱን ሁለቱም ወገን በበላይነት ለማጠናቀቅ ሲሉ የሰው ማዕበል ስልት (human wave strategy) እየተከተሉ እንደሆነ ነው:: ይህ ማለት ደግሞ ከፍተኛ የሰው ሀይል መስዋዕትነት በመክፈል በሌላኛው ወገን የተያዙ ቀጠናዎችን መቆጣጠር ነው:: በዚህ አይነት ጦርነት የሚሳተፍ የትኛውም ወታደር ተልዕኮው ‘አጥፍቶ የመጥፋት’ እንጂ ተመልሶ ቤተሰብ ለማየት እበቃለው ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው የሚሆነው:: ስለዚህ ወደዚህ ጦርነት በፍቃደኝነት ለገንዘብና ለጥቅማጥቅም ብሎ የሚዘምት የትኛውም የዎላይታ ወታደር የጀግና ሞት ሳይሆን የቅጥረኛ ወታደር ሞት እንደሚገጥመውና ሬሳውም የአሞራና የአራዊት መጫወቻ እንደሚሆን አውቆ ነው መግባት ያለበት::

ይኸው የእርስ በርስ ጦርነት እንዴት ተጀመረ ወይንም ማን ጀመረው አሊያም አላማው ምንድነው የሚለው ሳይሆን እስካሁን በዚህ ጦርነት ከሁለቱም ወገን ካለቁ ኢትዮጵያዊያን: ከደረሰው የሀገርና የህዝብ ሀብት ውድመት: እንዲሁም ከተከሰተው ሰብአዊ ቀውስና ከሚፈጥረው ቀጣይነት ያለው ሀገራዊና ቀጠናዊ የፖለቲካ አለመረጋጋት አንፃር በሰላማዊ አማራጮች መቋጨቱ ነው ፋታ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው:: በእንደዚህ አይነቱ ጦርነት የተዳከመች እና ለውጭ ጠላቶች ጥቃት ተጋላጭ የሆነች ኢትዮጵያ ለእኛም ሆነ ለጎረቤቶቻችን ሸክም እንጂ መከታ ልትሆን አትችልም:: ስለዚህ የዚህ ጦርነት ከበሮ መቺዎች በዚህ አስከፊ የጦርነት እሳት ላይ ተጨማሪ ማገዶ ለመጨመር ከመሯሯጥ ይልቅ ነገሮች በሰላማዊ የድርድር አማራጮች በቶሎ እንዲያልቁ እና የህዝባችን ሰቆቃ እንዲያበቃ በቁርጠኝነት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት በጦርነት ውስጥም ቢሆን ካለ በሳል የፖለቲካ አመራር የሚጠበቅ ነገር ነው::

Wolaita Today
Wolaita Today
Wolaita Today