አሁንም ለድርድር እና ሁሉን ላሳተፈ ንግግር አልረፈደም!
ረድኤት ታምሬ ኦሸ (ዶ/ር)
ኅዳር 10 2013ዓ.ም
በጦርነት ይበልጥ የሚወሳሰብ እንጂ የሚፈታ ችግር አይኖርም። ከመቶ አመት በፊት የተደረጉ አንዳንድ የእርስ በእርስ ግጭቶቻችን ተጽእኖዋቸው አሁን ድረስ መስተጋብራችንን እንዳወሳሰበው አለ። በዚህ ላይ አዲስ ጠባሳን መጨመር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ካልሆነ በስተቀር የሚያመጣው መፍትሄ አይኖርም። ይሄን ጦርነት በተመለከት አንዳንድ ጥያቄዎችን ለማንሳት እንገደዳለን
- ለጦርነቱ መጀመር መንስኤ የሆነው የሰሜን እዝ በህወሀት መጠቃቱ ነው የሚል ምክንያት ቀርቧል። ይህ ከሆነ ዘንድ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን ነው። የክልል ልዩ ሀይሎች የራሳቸውን ክልል ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ የማጥቃት እና “ግዛት የማስለቀቅ” እርምጃ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለምን ተደረገ?
- አንዳንዶች (high profile ያላቸውን ፖለቲከኞች ጨምሮ) ርስት የማስመለስ አጋጣሚ እንደሆነ በግልጽ እያወጁ ነው። በክልሎች መሀከል contested የሆነ ግዛት ካለ የሚመለስበት ህጋዊ አግባብ አለ። ነው ወይንስ መንግስት የሌለበት ጉልበት ያለው ሁሉ ያሻውን የሚያደርግበት “wild west” ውስጥ ነው የምንገኘው? የዚህ precedenc በጣም አደገኛ ነው!
- “ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ርስታችን ናት ፣ ብሄር እና መሬት መተሳሰር የለባቸውም” እያለ ሲያደነቁረን የነበረው ጭምብላም ሀይል ከምኔው ከአንድ ብሄር ክልል ላይ የተቀነሰ ርስት አለ እና ለማስመለስ ተረባረቡ ወደሚል ዘመቻ ገባ? ታዲያ ሌላውስ በገዛ ርስቱ እራሱን እንዳያስተዳድር፣ በራሱ ቋንቋ እንዳይሰራ፣ እና እንዳይዳኝ ነጋ ጠባ የቁራ ጩኅት ማሰማት ስለምን አስፈለገ?
ይሄ ጦርነት እንደታሰበው በአጭሩ የሚቋጭ ሳይሆን ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ሁሉንም የሚያስከፍል ነው። ኤርትራ በእዚህ ጦርነት ውስጥ አብይም ይሁን የአማራው ሀይል፣ እንዲሁም ህወሀት ተዳክመው እንዲወጡ እንጂ የትኛውም በቀላሉ አሸንፎ ፈርጥሞ እንዲወጣ አትፈልግም። ስለዚህም ተሳትፎዋ እጅግ በጣም የተመጠነ ብቻ ነው የሚሆነው። የኢሳያስ ግብ በተዳከመች ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ጀምሮ እየዘረጋው ባለው የ “ቀንዳቢ” እና የደህንነት መረብ አገሪቱን በመቆጣጠር ኢኮኖሚውን መበዝበዝ ነው ። የኢሳያስ አይኖች አሻግረው የሚያማትሩት የሲዳማን፣የወለጋን፣የጅማን ቡናዎች ነው። “ህወሀትን እንጨርሰው እንጂ ሌላው ገብስ ነው” ያሉት ሀይላት ተጠናክረው እንዲወጡ ኢሳያስ በፍጹም አይፈልግም። የሁሉም እኩል መዛል ለእርሱ አላማ ይበልጥ ምቹ ነው። ኢሳያስ ከዚህ የተለየ ኢትዮጵያን የመጥቀም አጀንዳ አለው ወይንም በእርሱ እገዛ አላማችን ይሳካል ብለው የሚያስቡ ካሉ ቆም ብለው እራሳቸውን እንዲመረምሩ ይመከራሉ። አሁንም ለድርድር እና ሁሉን ላሳተፈ ንግግር አልረፈደም!