በማህበራዊ ሚዲያው ግጭቱን ቤንዚን_እየጨመሩ ሌላ መልክ እንዲይዝ ማድረጉ ይጠቅም ይሆን?

Wolaita Today

በራፍኤል አዲሱ

ጥቅምት 26 2013ዓ.ም

ጦርነቱ ከህወሓት ቡድንና ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር ነው ብላች እራሳችሁን የምታሞኙ ሰዎች ፈጣሪ ይርዳችሁ:: እየተዋጋ ያለው መከላከያ ሰራዊት የአንዳችን ወንድም: የሌላኛችን አጎት ወይም የቅርብ ጓደኛ እና ዘመድ ሊሆን ይችላል:: በሌላኛው ወገን የተሰለፈውም ላለፉት ሃያ ምናምን አመታት በተለያዩ የሀገራችን ህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ በሰራው ስራ የተነሳ ጥላቻን ያተረፈው የህወሓት ቡድን አይደለም:: ይልቅ ነገ ይጦረኛል ብላ ወገቧ እስኪጎብጥ ለፍታ ያሳደገችው ግን ደግሞ እንደማንኛዋም ኢትዮጵያዊ እናት እስከዛሬ በድህነት የምትማቅቀው ትግራዋይ እናት ባለብሩህ ተስፋ (የነበረ) ለጋ ወጣት ልጅ እንጂ:: እሱኛው የህወሓት ቡድንማ ጦር ሜዳ መሄድ አይጠበቅበትም: ከተሽከርካሪ ወንበሩ ምቾት ቁጭ ብሎ ትዕዛዝ መስጠት ብቻ እንጂ::

 

በሌላ ጎኑ የአማራ ክልል ልዩ ሀይል ከትግራይ ክልል ጋር ጭቅጭቅ የሚፈጠርባቸውን ወልቃይት አይነት አከባቢዎች በዚህ አጋጣሚ ለማስመለስ ወደ ጦርነቱ መቀላቀሉ ይታወቃል:: ይህን ለማድረግ ግን መስዋዕትነት አይከፈልም ማለት አይቻልም:: ነገር ግን ይኼ የክልሉ እርምጃ ከህወሓት ይልቅ ከሰፊው የትግራይ ህዝብ ጋር ፀብ ውስጥ እንዲገባ እና ከፖለቲካ ቡድኖች መሀከል ካለ ቁርሾ አልፎ ወደ ህዝብ ለህዝብ የእርስ በርስ ግጭት ሊያመራ አይችልም ይሆን? የድንበር ጉዳዩስ ቢሆኑ በትክክለኛው ግዜና ሰዓት በሰላማዊና ህጋዊ አካሄድ በሚመለከተው የመንግስት አካል ሊፈታ አይችልም ወይ? (በእንደዚህ አይነቱ ሂደት ሊፈታ የሚችል ከሆነ ደግሞ ለምን አላስፈላጊ መስዋዕትነትስ ይከፈላል?) መልሱን “ይኸኛው መንገድ ይበጀናል” ብለው አምነው ለገቡበትና ነገሩን በማህበራዊ ሚዲያ ቤንዚን እየጨመሩበት ወደማይፈለግ አቅጣጫ እየወሰዱት ለሚገኙ አካላት መተዉ ሳይሻል አይቀርም::

 

በፌዴራሉ መንግስት (ብልፅግና ፓርቲ) ለጦርነቱ መነሻ ምክንያት ተደርጎ የተሰጠው “በህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል ልዩ ሀይል የሰሜን ዕዝን የመከላከያ ሀይል ላይ ጥቃት በማድረስ ከባባድ የጦር መሳሪያዎችን ለመዝረፍ በመሞከሩ” እንደሆነ ተገልፇል:: በሌላ ጎኑ የትግራይ ክልል መንግስት (ህወሓት) ይህ እውነት እንዳልሆነ ገልፆ “ማዕከላዊው መንግስት ትግራይን በጦር ለመውጋት የፈጠረው pretext” እንደሆነ ለአለምአቀፍ ሚዲያዎች ገልፇል:: በሌላ በኩል መከላከያ አፀፋዊ እርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ የተሰጠው ድርጊት ተፈፀመ በተባለ በሰዓታት ልዩነት እኩለ ሌሊት ላይ እንደመሆኑ ስለዚሁ incident በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ የሆነ ነገር የለም: በመንግስት ሚዲያ ከተሰጠው የገዢው ማዕከላዊ መንግስት መግለጫ ውጭ ማለት ነው::

 

አሁን የሚያሳስበው በዚህ ግጭት የተነሳ ግጭቱ መልኩን ቀይሮ ወደ ሰፋ የብሔር የእርስ በርስ ግጭት እንዳይሸጋገር እንዲሁም ወደ ሀገር አቀፍ የብሔር የእርስ በርስ ግጭትነት እንዳይሸጋገር ነው:: ይህ እንዲሆን ደግሞ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ሀገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩት ነገሮች በቂ የሆነ መሰረት የጣሉለት ይመስላል:: ብቻ ሀገራችን አሁን የገባችበት ምዕራፍ ለተዋናዮቹ ምክንያቱ ምንም ያክል “justified” ይሁን አስፈሪ ምዕራፍ ነው:: ምክንያቱ ደግሞ በግጭቱ በሁሉም የግጭቱ ተሳታፊ አካላት ‘የተመጠነ ሀይል’ የመጠቀሙም ሆነ በታጠቁ ሀይሎች መሀከል ብቻ አሊያም በአከባቢው ብቻ ሊገታ (contain ሊደረግ) የመቻሉ አዝማሚያ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነው::